መንግስት በገበያ ውስጥ ጣልቃ በመግባት መቆጣጠር አለበት-የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች

186

ሀዋሳ፤ መጋቢት 21/2014 (ኢዜአ)፡ መንግስት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለማርገም በገበያው ጣልቃ በመግባት ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል " ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ።

በአትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አረጋ ሹመቴ ለኢዜአ እንደገለጹት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የቆዩና እልባት ያላገኙ ችግሮች ናቸው።

ችግሩ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተባባሰ እንደመጣ የጠቆሙት ተመራማሪው፤ በተለይ በምግብ ነክና የዕለት ከዕለት ፍጆታ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎች ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመው፤ የተዛባ የግብይት ስርዓት መኖር፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ በገበያው ውስጥ ያሉ ህገ ወጥ ደላሎች ለችግሩ ዋነኛ  ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚጀመሩና ሳይጠናቀቁ የሚጓተቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ገበያው እንዲለቀቅ ማድረጋቸውና የኢትዮጵያ ብር ከዶላር አንጻር የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ መምጣቱ ለችግሩ ሌላው ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።

''ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ መፍትሄ ነው'' ያሉት  ዶክተር አረጋ ግጭት የሚስተዋልባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ አምራች በመሆናቸው በአካባቢዎቹ ያለው የጸጥታ ችግር ቅድሚያ ተሰጥቶት መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ የነጻ ገበያ ስርዓት ለማወጅ የሚያስችላት ደረጃ ላይ አልደረሰችም" ያሉት ተመራማሪው፤ ነጻ የገበያ ስርዓት ለመከተል በቂና ተወዳዳሪ አቅራቢ በብዛት መኖር፣ የተሳለጠ የግብይ ስርዓትና በቂ ተጠቃሚ መኖር እንደሚገባ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ መሰል ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የነጻ የገበያ ስርዓት  መታወጁን ጠቁመው፤ አሁንም ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከአርባምንጭ ከአርሶ አደሩ አንድ ኪሎ ሙዝ   በ12 እና 15 ብር ተገዝቶ ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ ከ40 ብር  በላይ እንደሚሸጥ በማሳያነት ያነሱት ተመራማሪው፤ ችግሩን ለመፍታት የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ  ተናግረዋል።

ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያና በማህበሩ የአጋርነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ስሜነህ ቤሲ በበኩላቸው ጦርነቱ፣ ድርቅና ኮቪድ 19 የዋጋ ግሽበትና ኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

''የዋጋ ግሽበትን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አይቻልም'' ያሉት ዶክተር ስሜነህ የግሽበት ምጣኔው ከአስር  በታች መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።

መንግስት ከምርጫ በፊት ቃል ከገባባቸው ጉዳዮች አንዱ የዋጋ ግሽበትን ከአስር በታች ማውረድ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ እየጨመረና የኑሮ ውድነቱ እየከፋ እንደመጣ ገልጸዋል።

የምግብ ምርቶች ላይ ከ35 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የጠቆሙት ዶክተር ስሜነህ፤ ይሄም  የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ አሳሳቢ እንዳደረገው ጠቁመዋል።

 የግብርና ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት መሆኑ  በጥናት መለየቱን ገለጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር አቅርቦትን ማሳደግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

 የምርት ግብዓት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መደጎም ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።

መታረስ ያለበትን ሰፊ መሬት በአግባቡ በማልማት ከቁጥቁጥ እርሻ መላቀቅና የሜካናይዜሽን እርሻን በስፋት ተግባራዊ  ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም