የስማርት የኤሌትሪክ ቆጣሪ አገልግሎት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ይተገበራል ተባለ

150
አዲስ አበባ ነሀሴ 30/2010 በነባር ቆጣሪዎች ላይ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ የታመነበት "ስማርት የኤሌትሪክ ቆጣሪ" አገልግሎት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ። አሁን አገልግሎት ላይ ያሉት ቆጣሪዎች ደንበኞች የተጠቀሙትን የሃይል መጠን በአግባቡ ያለመቁጠር፣ ለሃይል ስርቆት የተጋለጡና በከፍተኛ ደረጃ የሃይል ብክነት በማስከተል አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ ተጠቁሟል። ስማርት ቆጣሪው “አይቲ ፕላስ ስማርት ኢነርጂ ሜትር” በመባል የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ከሚሰራበት ቴክኖሎጂ በተሻለ ሁኔታ መስራት የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን አካቷል ተብሏል። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደመቀ ሮቢ ለኢዜአ እንደገለጹት  በቀጣዩ ዓመት 50 ሺህ ቆጣሪዎች ተገዝተው በሙከራ ደረጃ የተቋሙ ደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ደንበኞች ቤት ውስጥ ተተክለው ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል። ቆጣሪዎቹ በአገር ውስጥ አቅራቢዎች ተመርተው እንደሚቀርቡና በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም መጀመሪያ አቅራቢዎችን ለመለየት አገር አቀፍ ጨረታ አውጥቶ አምራቾች እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል። ጨረታው በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተጠናቆ አምራቾች ተለይተው ቆጣሪውን የማቅረብና የመትከል ስራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል። አንዳንድ የቆጣሪ አምራች ተቋማት ስማርት ቆጣሪውን በሙከራ ደረጃ እያመረቱ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ነባሩ ቆጣሪ አንባቢ ቆጣሪ በሚያነብበት ወቅት ስህተት እንደሚሰራና በተነበበው መሰረት የደንበኛ የመረጃ ቋት ውስጥ ገብቶ ትክክለኛ የክፍያ ደረሰኝ ለማውጣት አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ ምክትል ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙት ቆጣሪዎች ያለሰው ንክኪ ከዋና ማዕከል ጣቢያ ጋር በርቀት መቆጣጠሪያ እየተገናኘ የሚሰራበት እንደሆነም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት። በዚሁ መሰረት የሃይል ስርቆት ቢኖር በዋናው ማዕከል በሚገኝ የመረጃ ቋት ማወቅና እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና በአገልግሎት ሒሳብ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ብክነቶችና የሃይል መቆራረጥን እንደሚቀንስ አስረድተዋል። በተጨማሪም ቆጣሪ አንባቢ ወደ ደንበኛው ሳይሄድ ደንበኞች የራሳቸውን ሂሳብ አውቀው እንዲከፈሉ እንደሚያስችል ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ደረጃ የ"ስማርት የኤሌትሪክ ቆጣሪ" አገልግሎቱን በሙከራ ደረጃ በመጀመር በሙሉ ትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመገምገም በአገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ 250 ሺህ "ስማርት የኤሌትሪክ ቆጣሪዎችን" በአገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ እንዲውል የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ ለዚህ ቆጣሪ አገልግሎት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሊያስፈልግ እንደሚችልና አገልግሎቱ ሲጨምር በጀቱ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። በአጠቃላይ ስማርት ቆጣሪው የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ለደንበኞቹ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያግዘዋል። ቆጣሪውን በሙከራ ደረጃ አገልግሎት ላይ ለማዋል ከኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮ መወሰዱን አብራርተዋል። ስማርት ቆጣሪዎቹ በአገር ውስጥ መመረታቸው ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ የሚገቡትን ቆጣሪዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚያስቀርም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም