የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ሙያዊ ብቃትን በማረጋገጥ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ በትኩረት ይሰራል

373

መጋቢት 20/2014 (ኢዜአ) የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ሙያዊ ብቃት በማረጋገጥ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራር የሙያ ብቃት ምዘናን አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር  ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩም ለመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ምዘና በመስጠት ብቃታቸውን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ህይወት ጉግሳ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን  በማረጋገጥ ረገድ የመምህራን እና  የትምህርት ቤት አመራር ሙያዊ ብቃት ማጎልበት ይገባል፡፡

በዚህም ለነባር መምህራን፣ ወደ ሙያው ለሚገቡ ጀማሪ መምህራን እና ለርዕሰ መምህራን፤  ከትምህርት ይዘትና ከማስተማሪያ ስነ-ዘዴ አንጻር ምዘናዎችን በመስጠት ክፍተቶችን ማመላከት የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ምዘናው ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ በመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ለሚሰሩ መምህራን ፤ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የሚሰሩ መምህራን ላይ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህም የመማር ማስተማሩ ስራ በተቀመጠው የጥራት ስታንዳርድ እንዲሆን ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የመምህራን የመመዘን ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንና ገልፀው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት 5 ሺህ የሚደርሱ መምህራን በራሳቸው ፍላጎት ምዘና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ2005 ዓም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 17 ሺህ 849 የሚሆኑ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት  መምህራን የጹሁፍ ምዘና መውሰዳቸውም ተገልጿል፡፡

ይህም በመዲናዋ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት መምህራን መካከል የ64 በመቶ ድርሻ አለው ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም