ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሊከፈት ነው

77
አዲስ አበባ ነሀሴ  29/2010 ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሊከፈት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ተቋሙ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለመክፈት የሚያስችለውን ፊርማ ተፈራርሟል። ስምምነቱን የተፈራረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ቀርጻ በመተግበር ውጤታማ የሆነችና ዘላቂ ልማትና አረንጓዴ ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ያሳየች ፊታውራሪ መሆኗን ተናግረዋል። ተቋሙ ጽህፈት ቤቱን ለመክፈት መፈራረሙ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ውጤት ምስክር መሆኑን ገልጸዋል። የተቋሙ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ መሆኑ አገሪቱ በአፍሪካ ደረጃ እንዲሁም በዓለምአቀፍ መድረኮች ለአረንጓዴ ልማት  የነበራትን የመሪነት ሚና እንደሚያጎላው ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የተቋሙ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ  ስራ አስኪያጅ  ዴክሲፖስ አጉሪደስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የተቋሙ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት እንድታስተናግድ የተመረጠችው በአፍሪካ ብሎም በዓለምአቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆኗ ነው፡፡ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አገሪቱ የጀመረችውን ዘላቂ ልማት በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ጠንካራ፣ አካታችና ዘላቂ ልማት በታዳጊ አገሮች እንዲመጣ ድጋፍ የሚያደርግ፣ 27 አገሮችን በአባልነት ያቀፈ ዋና መስሪያ ቤቱን በደቡብ ኮሪያ ሴዑል ያደረገ የበየነ-መንግስታት ተቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተቋሙ መስራች ሀገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም