የመንግስት ግጭት የማቆም ውሳኔ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በማስገንዘብ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ተመዝግቦበታል

102


መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግስት ግጭት የማቆም ውሳኔ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል የተመዘገበበት መሆኑን አዲስ የተሾሙ አምባሳደሮች ገለጹ።


መንግስት በቅርቡ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ያለምንም ችግር ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እየገለጸ ይገኛል፡፡


ኢዜአ ያነጋገራቸው አዲስ የተሾሙ አምባሳደሮች እንደሚሉት፤ ውሳኔው ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ጽኑ አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስገነዘበ ነው፡፡


በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ፤ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን ምእራባዊያን እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል፡፡


መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን ተከትሎ ግን አንዳንድ የምእራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ በመግባት ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ ሲከተሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡


እነዚህ አገራት የኢትዮጵያን እውነት ወደ ጎን በመግፋት ለአሸባሪው ህወሓት ያደላ አካሄድ ሲከተሉ እንደነበርም ነው ያብራሩት፡፡


በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው፤መንግስት በአገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤በወቅቱ ጉዳዩን በሚመለከት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡


ሆኖም አንዳንድ ምእራባዊያን ይህንን ጥረት ችላ በማለት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲፈጥሩ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡


መንግስት አሁንም ለሰላም ፅኑ አቋም እንዳለው ሰሞኑን በወሰደው የግጭት ማቆም እርምጃ ዳግም ማረጋገጡንም ነው አምባሳደሮቹ የተናገሩት፡፡


በዚህም ምዕራባውያንን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለውሳኔው ድጋፍ ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ይህም መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም በማስገንዘብ የዲፕሎማሲ ድል እንደተገኘበትም ነው ያብራሩት፡፡


ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ የምትሻገርና በቀላሉ የማትንበረከክ ሀገር መሆኗን የገለጹት አምባሳደሮቹ፤ይህም ከኢትዮጵያ ጋር በኃይል ሳይሆን በስምምነት መስራት እንደሚገባ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል በመሻገር ጠንካራ መንግስት እንዲሁም ለአገር ሉዓላዊነት በአንድነት የሚቆም ህዝብ እንዳላት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት ችላለች ነው ያሉት፡፡


በዚህም ኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድል አስመዝግባለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም