ካናዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጀውን ‘ኤችአር6600’ ረቂቅ ሕግ በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ተጠየቀ

82

መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ካናዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጀውን ‘ኤችአር6600’ ረቂቅ ሕግ በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም የኢትዮ-ካናዳውያውን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ጥሪ አቀረበ።

ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ፍላጎትን በኃይል የመጫን አላማ ያለው ነው ብሏል።

ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን (ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር6600 ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

በካናዳ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ፍላጎትን በኃይል እንዲጫን የሚያደርግ ነው የሚል አቋም እንዳላቸው ኢክናስ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሕጉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተቀባይነት ካገኘ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ገልጿል።

‘ኤችአር6600’ ኢትዮጵያ ላይ የከፋ ማዕቀብ በመጣል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ሕወሓት ፍላጎቶች የሚያሳካና የሚጠቅም እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።

የተረቀቀው ሕግ ሕወሓት የሰብአዊነትና ሰብአዊ መብት ሕጎችን በመጣስ በግልጽ በፈጸማቸው ወንጀሎች ተጠያቂ እንዳይሆን የሚያደርግና በጦርነቱ ለአስከፊ ጉዳት  የተዳረጉ ዜጎችን ሕይወት ለባሰ ቀውስ ይዳርጋል ብሏል።

ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎቶችና ሉዓላዊነት ወደ ጎን የገፋ ነው፤ ሕጉ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከተፈረመ አደጋ የሚያንዣብብበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲያመራ ያደርጋል ብሏል። 

ኢክናስ ‘ኤችአር6600’ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት እንደሚጎዳ አመልክቷል።

ሕጉ የኢትዮጵያ መንግስት ግጭት በማቆም ሰላም ለማምጣት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ያላገናዘበ መሆኑን ገልጿል።

‘የፖለቲካ እስረኞች’ በመፍታትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት የወሰዳቸውን እርምጃዎችና የሰላም ጥረቶች ረቂቅ ሕጉ ሊያያቸው እንዳልፈለገ ኢክናስ ገልጿል።

‘ኤችአር6600’ አሜሪካ አጋሮቿን በማስተባበር ኢትዮጵያ የፋይናንስ ገደብ እንዲጣልባት የሚያቀርበው ምክር ሀሳብ አደገኛ እንደሆነና እድሜያቸው በገፉ ሰዎች፣ ሴቶችና ሕጻናት ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ አመልክቷል።

ካናዳ ይሄን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ኢክናስ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም