በደቡብ ክልል እናቶች በጤና ተቋም የመውለድ ልምድን እንዲያዳብሩ የተደረገው ጥረት ውጤት አምጥቷል

78

ዲላ ፤ መጋቢት 17/2014 (ኢዜአ) እናቶች በጤና ተቋም የመውለድ ልምድን እንዲያዳብሩ የተደረገ ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ ።

ጤና ቢሮው በዲላ ከተማ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ  የምክክር መድረክ  አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንደገለጹት፤  ባለፉት ስድስት ወራት እናቶች በጤና ተቋም መውለድ ልማድ እንዲያዳብሩ በተደረገ ጥረት ከ188 ሺህ 605 በላይ እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ በጤና ተቋም መወለድ ችለዋል።

በዚህም በክልሉ በሰለጠነ ባለሙያ የሚደረግ የወሊድ  ምጣኔን ከ74 ወደ 80 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ከእናቶች ወልድ በተጓዳኝ በጤና መድን አገልግሎት ሸፋን ፣በክትባት አገልግሎትና በሌላም የጤና ልማት ዘርፍ ስኬታማ   ሰራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ሆኖም በመረጃ ጥራት፣በግብዓት እጥረትና በአንቡላስ አገልግሎት እንዲሁም በድንገተኛ ህክምና የታዩ ማነቆዎችን በማስተካከል በቀጣይ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን  አመላክተዋል።

በተፈለገው ልክ ለህሙማን ህክምና ለመስጠት በተለይ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ላይ የግብዓት እጥረት ማነቆ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በጎፋ ዞን ሳውላ ጀነራል ሆስፒታል ሃላፊ ዶክተር ግዛቸው ቦሎ ናቸው።

በተለይ አሁን ላይ በሆስፒታል ለመውለድ ያለው ፍላጎት ከፍ እያለ ቢመጣም የህክምና ግብዓት እጥረትና የአንቡላስ አገልግሎት መቆራረጥ ትኩረት ተሰጥቶ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ልዩ ሆስፒታል ሃላፊ ዶክተር ሉቃስ ዲንጋቶ በበኩላቸው፤ የጤና መድህን አገልግሎት ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በተቋሙ አገልግሎት  የሚጠቀመው ህብረተሰቡ መጨመሩን ገልጸዋል።

ይሁንና በመድሃኒትና ሌላም ግብዓት እጥረት ተገቢውን አገልግሎት የማያገኝ ከሆነ በጤና መድህን  ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ልታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሀገራዊ ነባረዊ ሁኔታ በህክምና ግብዓቶች ላይ ጫና ማሳደሩን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት የሴቶችና ህጻናት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወላይቴ ዳቴ ናቸው።

ችግሩን ለመቀነስም በቅድመ መከላከልና በተገልጋይ እንክብካቤ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የሆስፒታል ሥራ አስኪያጆች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመድረኩ  ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም