የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

154

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከቀያቸው ለተፈናቀሉና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ የሊጉ አባላት የተሰባሰበ ሲሆን የምግብ ነክ፣ የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ አልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና የሕክምና ቁሳቁሶች ያካተተ ነው።

ድጋፉንም የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወጣት አክሊሉ ታደሰና የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መለስ አባተ ለደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ መኮንን አስረክበዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት መለስ አባተ፤ የሊጉ አባላት በህልውና ዘመቻው ወቅት ግንባር በመዝመት፤ አካባቢን በንቃት በመጠበቅ እንዲሁም ከኋላ ደጀን ሆነው ሃብት በማሰባሰብ ድሉ እንዲመዘገብ አድርገዋል ብሏል።

አሁን ላይ ደግሞ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማት በተሻለ አደረጃጀት እንዲገነቡ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመርዳት የምግብ፣ አልባሳትና የሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ማስረከቡን ገልጿል።

የወጣቶች ሊግ ዋነኛ ዓላማ የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት በመሆኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ጠቁሟል።

የብልጽግና ፖርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አክሊሉ ታደሰ፤ በአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የተደረገው ድጋፍ ከቁሳቁሱ በላይ የአብሮነት ትርጉም አለው ብሏል።

ድጋፉ የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን አንድነት፣ ፍቅር፣ አብሮነትና መተሳሰብ ጭምር የታየበት ነው ብሏል።

ወጣቶች የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፋንታ በእጃቸው ላይ መሆኑን ተረድተው እንቅስቃሴዎቻቸውን በሰከነና ወንድማማችነትን በሚያጎለብት መንገድ ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ መኮንን በጦርነቱ የወደሙ በርካታ ተቋማት በመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ይህም የሆነው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመሆን ድጋፍ በማድረጋቸው  መሆኑን ጠቅሶ፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም