ዩኒቨርስቲው በሥራ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

375

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

በኸልት ፕራይዝ ፋውንዴሽንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋራ የሚካሄደው የተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።


ኸልት ፕራይዝ ፋውንዴሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተማሪዎችን የሚያሳትፍ የቢዝነስ ውድድር ሲሆን ተማሪዎች በቡድን ያላቸውን ኃሳብ ወደ ቢዝነስ የሚቀይሩበት መድረክ ነው።


ፋውንዴሽኑ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በቴክኖሎጂ 30 የሥራ ፈጠራ ኃሳብ ያላቸው የተማሪዎች ቡድን አወዳድሯል።


በኸልት ፋውንዴሽን የዘንድሮ ለቢዝነስ የሥራ ፈጠራ ውድድር 137 የፈጠራ ኃሳቦች መመዝገባቸውን የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30ዎቹ ተለይተው እንዲወዳደሩ ተደርጓል።


ከእነዚህም መካከል ደግሞ እንደገና 12 ተማሪዎች የተለዩ ሲሆን ዛሬ ባደረጉት የማጠቃለያ ውድድር ሦስት ቡድኖች የውደድሩ አሸናፊ ሆነው ከፋውንዴሽኑ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።


የመጀመሪያው ቡድን ለዩኒቨርሲቲዎች የምግብ አቅርቦት የሥራ ፈጠራ የተወዳደሩ ሲሆኑ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእጅ የተሰሩ የቤት ውስጥ መገልገያ ምርት ያቀረቡ ተማሪዎች ናቸው።


የወዳደቁ ፕላስቲኮችን መሰብስብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ያቀረቡ የተማሪዎች ቡድን ደግሞ የኸልት ፕራይዝ ፋውንዴሽን የሦስተኛ ደረጃ ተሸላሚ መሆን ችሏል።


አንደኛ የወጣው ቡድን ኢትዮጵያንና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ32 ከተሞች ከሚዘጋጁት አንዱ ከተማ ላይ እንዲወዳደር እድል ተመቻችቶለታል።


ቡድኑ ይህንንም ዓለም አቀፍ ውድድር ማለፍ ከቻለ በቀጣይ በአሜሪካ ኒውዮርክ ግዛት በሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ለአንድ ሚሊዮን ዶላር የሚወዳደሩ ይሆናል ተብሏል።

ዓለም አቀፍ ውድድሩ ከቢዝነስ ኃሳብ ጎን ለጎን ተማሪዎች የመሪነትና የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ እንደሚያደርግም የፋውንዴሽኑ አስተባባሪ አቶ ኪሩቤል እንግዳወርቅ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪ ትሥሥርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሹሜይ በርሄ ውድድሩ ዩኒቨርስቲው ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር ያስችላል ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሸጋገር የሚደረገውንም ጥረት ለማሳለጥም ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።


የሥራ ፈጠራ ላይ የተወዳደሩት ኃሳቦች በዩኒቨርስቲው የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከሉ ላይ አገልግሎት በመሥጠት ወደ ገበያ እንዲገቡ እንደሚደረግም ተናግረዋል።


ወጣቱ ትውልድ ፈጠራንና ቴክኖሎጂን ወደ ኅብረተሰቡ አቅርቦ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታበትን ጥረት ዩኒቨርስቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ኸልት ፕራይዝ ፋውንዴሽን በዓለም አቀፍ የመሪነት ቦርድ ላይ ሦስተኛው ምርጥ ተመዝጋቢ የትምህርት ተቋም ነው።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም