ኦልማ ትምህርት የትውልድ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ዘርፉን እያገዘ ነው- አቶ አባዱላ ገመዳ

97

ጅማ ፣መጋቢት 17/2014( ኢዜአ) የኦሮሚያ ልማት ማህበር ትምህርት የትውልድ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ዘርፉን እያገዘ ነው ሲሉ የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ አስታወቀ።
 

ማህበሩ በጅማ ዞን ሸቤ ወረዳ በ10 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ልዩ ትምህርት ቤት ዛሬ አስመርቋል ።

ትምህርት ቤቱ በ55 ቀን ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑ ተመላክቷል ።

የኦሮሚያ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ  በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት  ልማት ማህበሩ ትምህርት የትውልድ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የዘርፉን ልማት እያገዘ ነው ።

ማህበሩ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ልማት ማህበሩ የሚገነባቸው ትምህርት ቤቶችን በቦታው ሆኖ ስለሚከታተል በመጠነኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ውስጥ  የሚጠናቀቁ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ለልዩ ትምህርት ቤቱ 35 ኮምፒተሮችን ማበርከቱን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ልማት ማህበር ለወደፊትም በክልሉ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የሚሰራ መሆኑን አቶ አባዱላ አስታውቀዋል።

የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው "መንግስት ለትምህርት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ የኦሮሚያ ልማት ማህበር የሚያደርገው ድጋፍ የሚደነቅና ሊበረታታ የሚገባው የልማት ተግባር ነው" ብለዋል።

"ማህበሩ ለዞኑ የትምህርት መሰረተ ልማት መስፋፋት ላበረከተልን ትልቅ የትውልድ ስጦታ በህዝቡ ስም እናመሰግናለን" ብለዋል።

ልዩ ትምህርት ቤቱ ለመማሪያ፣ ለቤተ -መጻህፍት፣ ለቤተ- ሙከራ፣ ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ለአስተዳደር አገልግሎት መስጫዎች የሚሆኑ አራት ብሎኮች ያሉት መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በኦሮሚያ ልማት ማህበር  የፕላን ክፍል ሀላፊ አቶ አብዱለዚዝ አህመድ ትምህርት ቤቱ በ10 ሚሊዮን ብር የተገነባ መሆኑን ጠቁመው ወንበር፣ ኮምፒውተሮችና የቤተ- ሙከራ ቁሳቁስ የተሟላለት መሆኑን ተናግረዋል ።

"ማህበሩ እስካሁን በክልሉ 889 አዲስ ትምህርት ቤቶችንና ከ1 ሺህ 600 በላይ ተጨማሪ ክፍሎችን በመገንባት የትምህርት ዘርፋን እየደገፈ ነው" ብለዋል።

 በልዩ ትምህርት ቤቱ ምረቃ ስነ ስርአት ላይ  የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚና የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ጨምሮ  የሀይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሌላ ልማት ማህበሩ በሸቤ ወረዳ  ለሚያስገነባው የቡኡረ ቦሩ መዋእለ ህጻናት ትምህርት ቤት አቶ አባዱላ ገመዳ  የመሰረት ድንጋይ  አስቀምጠዋል።

የመዋእለ ህጻናት ትምህርት ቤቱ ግንባታ በመስከረም 2015 ዓም የሚጀመር መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱለዚዝ የግንባታው ሙሉ ወጭ በልማት ማህበሩ የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል ።

በተጨማሪም የትምህርት ግብአቶች የሚሟላለት መሆኑን ጠቁመው ማህበሩ ላጠቃላይ ወጭው እስከ 5 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚመድብ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም