አገር በቀል የውይይት እሴቶችን በግብዓትነት በመውሰድ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እየተሰራ ነው

70


መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)አገር በቀል የውይይትና የምክክር እሴቶችን በግብዓትነት በመጠቀም ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ።


የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።

በዋናነትም ቢሮ ማደራጀት፣የሥራ መመሪያ ማዘጋጀት፣ የኮሚሽነሮች ሥራና ተልዕኮን መለየት፣ እቅድ ማቀድና ለምክክሩ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን ማሰባሰብ ዋነኞቹ ናቸው።


በተለይም ለምክክር ሂደት ጠቃሚ የሆኑ አገር በቀል እሴቶችንና የሌሎች አገራት ተሞክሮዎችን በግብዓትነት የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።


ይህንንም ተከትሎ በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ያለምንም የውጭ ጣልቃገብነት የአገር ውስጥ የውይይትና የምክክር እሴቶችን ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ኮሚሽኑ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ለምክክሩ የሚረዱ ጠቃሚ ግብዓቶችን ለመውሰድና በጋራ ለመሥራት ዝግጅት ማደረጉን ጠቁመዋል።

የቱለማና የኦሮሞ አባገዳ ኅብረት ጸሐፊ ጎበና ሆላሬሶ በኢትዮጵያ ሁሉም ብሔሮች የሚገጥሟቸውን ውስጣዊ ችግሮች የሚፈቱበት የራሳቸው እሴት መኖራቸውን ተናግረዋል።

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የገዳ ሥርዓትም በምክክርና በውይይት የማይፈታ ችግር አለመኖሩን ጠቁመው፤ይህንን እሴት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ይህንንም ተሞክሮ በመውሰድ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ልዩነቶችን ለማስታረቅና ዜጎችን የሚያግባቧቸውና የሚተማመኑባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላል ይላሉ።


የወላይታ አገር ሽማግሌ ሰይፉ ለታ በበኩላቸው፤ በየአካባቢው የወላይታ ብሔረሰብ በየቀዬው የሚፈጠሩ ችግሮች የሚፈታበት ባህላዊ ሥርዓት እንዳለው ይናገራሉ።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ይህንንና ሌሎችም ኢትዮጵያዊ ባህላዊ የችግር አፈታት ዘዴዎችና የውይይት እሴቶችን በመጠቀም ሥራውን ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በሚያካሂዳቸው የምክክር ሂደት ውስጥም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ለማርገብና ለመፍታት አካታች አገራዊ የሕዝብ ምክክር ለማድረግ አስፈልጓል።


ይህንንም ተከትሎ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሰረት፤ አገራዊ ምክክሩን በገለልተኝነት የሚያስተባብርና የሚመራ ተቋም በማስፈለጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አቋቁሟል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም