የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ የልማት ሥራዎች ላይ አተኩረን እንሰራለን--- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

84

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 17/2014(ኤዜአ) የክልሉን ሰላም በተሟላ ሁኔታ በማረጋጋጥ የልማት ሥራዎች ላይ አተኩረን እንሰራለን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት ማምሻውን በተጠናቀቀበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፤ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመቋቋም የክልሉ ኢኮኖሚ በከፋ ሁኔታ እንዳይጎዳ ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይ ፅንፈኛ ሃይሎችን በመታገል ክልሉ ወደ ባሰ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባና ሰላም እንዲመጣ በማድረግ በኩል መልካም ሥራ መከናወኑን ነው የተናገሩት።

በቀጣይ ወራትም ክልሉን ወደ ተሟላና የተረጋጋ ሰላምን በማረጋጋጥ  ልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ይበልጥ አተኩረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

"ለዚህም በክልሉ ያለውን የውሃ ሃብትና መሬት በቴክኖሎጂ ታግዘን በማልማት ህዝባችንን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረን ለመስራት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

አሁን ያለው ዓለም ዓቀፋዊና አገራዊ ሁኔታ ለማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር ፈተና ቢሆንም አርሶ አደሩ ሌሎች የምርት ማሳደጊያ አማራጮችን አሟጦ እንዲጠቀም ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚገባ አመልክተዋል።   

"የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ዕጥረት ለማቃለልም አርሶ አደሩ እና ባለሃብቱ ተቀናጅቶ ዋና ዋና የሰብል ዘሮችን በማባዛት እጥረቱ እንዲቃለል ይሰራል" ብለዋል።

የእርሻ መካናይዜሽንን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት ማቅረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።   

እንደ ሀገር የተስተዋለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመሻገር ህብረተሰቡ የቆየ የመተባበርና የመረዳዳት ባህሉን ሊያጎለበት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።

በወቅታዊ ችግሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች የእለት ምግብ እንዲደርስ ከማድረግ ጎን ለጎን ለመልሶ ማደራጀትና ማስፈር ስራው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በመሰረተ ልማት በኩልም ተጀምረው እስካሁን ያልተጠናቀቁ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የመስኖ ግንባታ ሥራዎችና የሥራ አጥነት ችግሮች እንዲቃለሉ  የክልሉ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ የምክር ቤት አባላትም በተመረጡበት አካባቢ ህብረተሰቡን በማስተባበር፣ አስፈፃሚ አካላትን በመቆጣጠርና በመከታተል ልማት ከማፋጠን ባለፈ ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አመልክተዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት በመንግስት ተቋማት ህዝቡን ለምሬት እየዳረገ የሚገኘውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሪፎርም ሥራ በቀጣይ ይከናወናል።

የክልሉ ምክር ቤት  መደበኛ ጉባኤ የአስተዳደሩን የግማሽ ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ በአብላጫ ድምፅ በማፅደቅ እንዲሁም  የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠትና የቋሚ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ  የሁለት ቀናት መረሃ ግብሩን  አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም