በሐረሪ ክልል የተጀመረው የቅዳሜ ገበያ አምራችና ሸማቹን በማገናኘት ገበያውን ለማረጋጋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል

86

ሐረር ፤ መጋቢት 17/2014(ኢዜአ) የተጀመረው የቅዳሜ ገበያ አምራችና ሸማቹን በማገናኘት ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪ ለማሰቀረትና ገበያን ለማረጋጋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር  የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በክልሉ የቅዳሜ የጎዳና ላይ  ገበያ ዛሬ ተመርቆ  በይፋ በተጀመረበት ወቅት  ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፤ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ሚዛናዊ ለማድረግ  ምርትን ማሳደግ ያስፈልጋል፤ ለዚህም  አምራቹ ምርቱን በማቅረብ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

አምራቹ ከሸማቹ ጋር መገናኘቱ ደግሞ ያለአስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን ያስቀራል ብለዋል ።

ደላሎች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ይፈጥራሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቅዳሜ ገበያው ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም አምራቹና ሸማቹ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲገበያዩ በማመቻቸት ደላሎችን ከመሀል ማስወጣት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም  አምራቹም ከምርቱ  የሚገባውን  እንዲያገኝ፤  ሸማቹም ፍትሀዊ በሆነ ዋጋ በመሸመት ሁለቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው፤የገበያ ስርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያንዳንዱ ተቋም የቤት ስራውን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ምርትን ያለአግባብ በሚያከማቹና  ያልተገባ የኑሮ ውድነት በሚፈጥሩ ስግብግብ ነጋዴዎችም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ፤ለገበያው የቀረበው የአርሶ አደሩ የመጀመሪያው የበጋ ምርት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም  አርሶ አደሩን እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል።

ምርቱ በክልል ብቻ ሳይገደብ በአጎራባች አካባቢዎች   ጭምር የሚቀርብበት ሁኔታ እንደሚመቻችም አስታውቀዋል ።

የቅዳሜ ገበያ ሻጭና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት የሁለቱም ወገን ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።

ከሸማቹ መካከል ወይዘሮ ሌሊሴ ደስታ ፤ በቅዳሜ ገበያ አርሶ አደሩና ሸማቹ በግንባር ተገናኝቶ መገበያየቱ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ ረድቶናል ብለዋል በሰጡት አስተያየት።

 የቅዳሜ ገበያ ቋሚ ሆኖ ቢሰራበት አርሶ አደሩንም ከምርቱ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ የሚያስችል ከመሆኑም  ባሻገር የገበያ ሁኔታውን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አቶ አብዱል አዚዝ ሀሺም በበኩላቸው፤  በቅዳሜ ገበያው ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታችን አስደስቶናል፤ ይህ መልካም ጅማሮ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

በተጨማሪ  የተጓደሉ  እንደ ምግብ ዘይትና ስኳር ያሉ ሸቀጦች በቅዳሜ ገበያው ላይ እንዲካተትም ጠይቀዋል ።

አርሶ አደር መፍቱሀ ሙሳ ፤ የቅዳሜ ገበያ ከሸማቹ ማህበረሰብ ጋር በቀጥታ እንድንገናኝ እድል የፈጠረ ነው፤ በዚህም ካሁን ቀደም ምርታችንን እንሸጥበት ከነበረው የተሻለ ዋጋ እያስገኘልን ነው ብለዋል።

ገበያው ደላሎችን ከመሀል በማስወጣት አምራቹን ከሸማቹ ጋር ያገናኘ መሆኑ በሁለቱም በኩል ተጠቃሚነታችንን አሳድጎታል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም