ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ ነገ ሰመራ ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ ነገ ሰመራ ይገባሉ
83
ሰመራ ነሀሴ 29/2010 ነገ ሰመራ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህን ለመቀበል ሲደረግ የቆየው ዝግጅት መጠናቀቁን የአፋር ክልሉ መንግሰት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰኢድ አሃው ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የአፋር መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ሱልጣን ሃንፈሬ አሊሚራህ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቀሴ በመደገፍ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የገቡት እየተገባደደ ባለው ወር መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱም የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመሄድ ደማቅ አቀባበል በማድረግ ለሱልጣኑ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም የክልሉ መንግስት ሱልጡኑ ወደ ሰመራ በሚመጡበት ወቅት ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶች አዋቅሮ ቅደመ-ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ሰኢድ አስታውቀዋል፡፡ አሁን የቅድመ-ዝግጅቱ ስራ በማጠናቀቅ ሱልጣኑን ለመቀበል እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ነገ ሰመራ እንደሚገቡ የሚጠበቁት የአፋር መንፈሳዊ መሪ ሱልጣን አሊሚራህ ሃንፌሪን የጎሳ መሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡ የሱልጣኑ መምጣት በክልሉ የተጀመሩ የሰላምና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተመልክቷል፡፡