የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት በእውቀትና ጥራት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተሰራ ነው

127

አዲስ አበባ  መጋቢት 16/ 2014 /ኢዜአ/ በአገር ዓቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት በእውቀትና ጥራት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በጤና ሚኒስቴር፣ 'ኤች.አር.ዲ.ዲ' የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና 'ጃፒያጎ' ኢትዮጵያ ትብብር ሀገር አቀፉን የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ የምክክር አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከጤና ማህበራትና ከሌሎች ተቋማትና የሙያ ማህበራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በዚሁ ወቅት በጤና ሚኒስቴር የሰው ኃብት ልማት ዳይሬክተሩ አቶ አሰግድ ሳሙኤል እንዳሉት የጤና ስርዓቱን በማሻሻል የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለመለወጥ እየተሰራ ነው።

ሚኒስቴሩም የጤና ስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ስዎች ትክክለኛ ብቃት ባለው የጤና ባለሙያ መታከም ስለሚገባቸው በተከታታይነት ሙያተኞቹን የማብቃት ስራ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የአማሪካ ተራድዖ ድርጅት (ዩ.ኤስ.አይ.ዲ) የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተሯ ዶክተር ህሊና ወርቁም እንዲሁ ይህን ጉዳይ ለጤና ሚኒስቴር ብቻ መተው አያስፈልግም ብለዋል።

የጤና ስርዓቱን የበለጠ ለማሻሻል የሙያ ማሕበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የዘርፉ አጋሮችና ለጋሾችም ሙያተኞች ተከታታይ የስልጠና ያገኙ ዘንድ የእውቀትና የገንዘድ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በ'ጃፒጎ ኢትዮጵያ' የጤናና የሰው ኃይል ማሻሻያ ፕሮግራም ዳይሬክተሩ ዶክተር ተግባር ይግዛው፤ የጤና ባሙያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሳደግ የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን ይገልጻሉ።

በቀጣይም የትምህርት ጥራትን ማሻሻል፣ የቁጥጥር ስርዓትን ማዘመን እና ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎችን ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የምክክር አውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም