በጌዴኦ ዞን ሕገወጥ ሆነው በተገኙ 820 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

139

ዲላ ፤ መጋቢት 16/2014 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ምርት በመደበቅ፣ አለአግባብ ዋጋ በመጨመርና ሌሎች ህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የተገኙ 820 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ።

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት፣ ስርጭትና በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችና መፍትሄው ላይ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የመምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምስጋና በራሶ፤ በዞኑ ህገ ወጥ ንግድ መንሰራፋት በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህንኑ ተከትሎ በየደረጀው ግብረ ሃይል በማቋቀም በንግድ ስርዓቱ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ አሰራሮችን በመለየት አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ እየተወሰደ ነው" ብለዋል ።

ባለፉት ሶስት ወራት በተደረገ ቁጥጥር ህገ ውጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በተገኙ 820 የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፤ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣ ከደረጃ በታች የሆነና ጊዜ ያለፈበት ምርት ለገበያ በማቅረብ፣ ፣ዘይትን ጨምሮ ምግብ ነክ ሸቀጦችን በመደበቅ በገበያ ላይ እጥረት በመፍጠር ህብረተሰቡ ላይ ጫና በማሳደራቸው እርምጃው ተወስዶባቸዋል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት ውስጥ 113 በፍርድ ቤት በተወሰነባቸው መሠረት ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ እንዲቀጡ መደረጉንና በቀሪዎቹ የንግድ ተቋማት ላይ የማሸግ፣ በህግ ተጠያዊ የማድረግና በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በህገ ወጥ ንግድ የሚሳተፉ አካላት የተጋነነ ትርፍ ለማግኘት ህብረተሰቡን በማማረር በመንግስት ላይ ጫና እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆኑን በመጠቆምም ህጋዊ ነጋዴዎች፣ የፀጥታ ሃይልና ሸማቹ ህብረተሰብ ህገ ወጦችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ አመልክተዋል።

የተጋነነ የዋጋ ጭማሪና የገበያ አለመረጋጋት ሽማቹን ህብረተሰብ ላልተገባ የኑሮ ጫና መዳረጉን የሚናገሩት ደግሞ የዲላ ከተማ የንግዱ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አረጋኸኝ አሰፋ ናቸው።

በችርቻሮ ከሚሰራው ነጋዴ ባለፈ አቅራቢው የገበያ ዋጋ በመወሰንና ምርት በመያዝ የገበያ ስርዓቱ እንዳይረጋጋ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አንስተው በተለይ የፋብሪካ ምርት ጅምላ ሻጮች ደረሰኝ አለመስጠት፣ ከሰጡም ከሸጡት ዋጋ ቀንሰው መቁረጥ፣ ምርት እያለ የለም ማለትና መሰል ችግሮች እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት በየደረጃው በንግድ ሰንሰለቱ ዙሪያ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ለማስቆም አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በበኩላቸው፤ በንግድ ሥርዓት ከህግ አግባብ ውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ንግድ ሥርዓትን ለማሻሻል ፣ የህግ ማዕቀፍና ፍታሃዊ የህግ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመው፤ ሽማቾች ከመገበያየታቸው በፊት ስለ አገልግሎቱና ዕቃው በቂና ትክክለኛ መረጃ መያዛቸውን እርግጠኛ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በምክክር መድረኩ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ የንግዱ ማህበረሰብና የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም