ቪኪ ፎርድ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንደሚደግፉ አስታወቁ

54

መጋቢት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደግፉ አስታወቁ።

በትግራይ በኩል ያሉ አካላት በበኩላቸው የተኩስ አቁም በማድረግና ከአፋር ክልሎች በመውጣት ለውሳኔው ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው በትዊተር ገጻቸው ባወጡት መልዕክት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እንዲደርስ በማድረግ ቁርጠኝነትን ማሳየት እንደሚገባ አመልክተው፤ የእንግሊዝ መንግስት በዚህ ረገድ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ አመልክተዋል።

የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ከዚህ ቀደም በጥር ወር አጋማሽ አሸባሪው ህወሃት በአባላ ከተማ የጀመረው ትንኮሳ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደናቅፍ ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ትናንት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

በመግለጫውም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ እንደሚገኝም ጠቅሷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም