‘ኤስ.3199’ ምን ይዟል?

380

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021’ ወይም ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ነው።

 ‘ኤስ.3199’ “አሜሪካ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት፣ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣትና የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የምታደርገውን የዲፕሎማሲ፣ የልማትና ሕጋዊ ድጋፍ ይበልጥ የማሳደግ አላማ ያለው ነው” ሲል በሕጉ መግቢያ ላይ ይገልጻል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነት ድጋፍ በጊዜያዊነት እንድታቆምና በኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲፈታና ሰላምን የማምጣት ጥረቶች እንድትደግፍ ሕጋዊ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን በሕጉ ላይ ተቀምጧል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፍ፣ ከጦርነቱ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ወይም በጦርነቱ ለሚሳተፉ አካላት የቁሳቁስ ድጋፍ በሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ሀሳብ ያቀርባል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በሕግ ሊጠየቁና ሊቀጡ እንደሚገባ በረቂቅ ሕጉ ተጠቅሷል።

ሕጉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ” በሚል ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ለመደገፍና ለማገዝ የወጣ እንደሆነ ከዚህ ቀደም የሕጉ አዘጋጅ የሆኑት ሴናተሮች ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል።

በአሜሪካ የሚገኘው ሲቪክ ተቋም ጌትፋክት ኤስ.3199 ሕግ ለኢትዮጵያ አደገኛ የሆነው ምንድነው? በሚል በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ  ሕጉ የተረቀቀው በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት የተዛቡ ዘገባዎችን መሰረት በማድረግ እንደሆነ ገልጿል።

ኢትዮጵያውያን ላለፉት 30 ዓመታት የሕወሓት የጭካኔ ሰለባ የሆነው እስከ ዛሬ ድረስ ቢቆይም፤ ሕጉ የሕወሓት ታጣቂዎችን ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

የሕጉ ረቂቅ ኢትዮጵያ ዜጎችን ከሕወሓት ሽብርተኝነት እንዳትከላከል እንደሚገድብና ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ሉዓላዊነትና ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አስታውቋል።

በተሳሳተ አላማ ላይ የተመሰረተ ረቂቅ ሽግ እንዳይጸድቅ ለማስቆም እርምጃ ካልተወሰደ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን ጉዳቶች ያመጣል ሲል ጌትፋክት ይገልጻል።

  • በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይጣላል፤ ኢትዮጵያን እንድትገለል የሚያደርግ ነው።
  • ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ እንዳይመጡ የቪዛ ቅነሳና ስረዛ ያደርጋል።
  • ሁሉንም የአሜሪካ ኢንቨስትመንቶችና የገንዘብ ልውውጦች ያግዳል።
  • አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የጸጥታና የልማት ድጋፍ ይገድባል።
  • አሜሪካ ተሰሚነቷንና ድምጽ የመስጠት መብቷን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ብድርና የብድር ማራዘሚያ ክልከላ እንዲደረግ ግፊት ታደርጋለች።
  • አሜሪካ ሕጉን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውትድርና ድጋፍ እንዲሁም ግዢ እንዳታገኝ ጫና ታሳድራለች።
  • አሜሪካ የዓለም አገራትና የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን በማስተባበር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ መገደብ ናቸው ሲል ጌትፋክት የገለጸው።

የሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በረቂቅ ሕጉ ላይ ትናንት ሊያደርግ የነበረውን ስብስባ ወደ መጋቢት 20 ቀን 2014  ዓ.ም ማራዘሙን  ገልጿል።

“በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮቻቸው በሆኑ የኮሚቴው አባላት ሴናተሮች ላይ ባደረጉት ግፊት የተወሰኑ ሴናተሮች ረቂቅ ሕጉን በደንብ ማየት እንደሚገባቸውና ጊዜ እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው ምክንያት ኮሚቴው በሕጉ ላይ ሊያደርግ የነበረውን ውይይት ወደ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ማራዘሙን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል አባል አቶ ከባዱ ሙሉቀን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰሞኑን ‘ኤስ3199’ ረቂቅ ሕግ የሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት አድርጎ ውሳኔ እንዳያሳልፍበት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሴናተሮችን በስልክ በማነጋገር ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ የተወሰኑ ሴናተሮች ጉዳዩን በደንብ እንዲያጤኑት አድርጓል ብለዋል።

ሴናተር ቲም ኬን (ቨርጂኒያ) እና ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን (ሜሪላንድ) ረቂቅ ሕጉ ላይ ዛሬ ለመወያየት ጊዜ እንደሚፈልጉ ጥያቄ ካቀረቡት የኮሚቴው አባላት ውስጥ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

“የውይይቱ መራዘም እስካሁን በተደረገው ጥረት የተገኘው ትንሽ ውጤት ነው፤ ውይይቱ ተራዘመ ማለት ረቂቅ ሕጉ አይጸድቅም ማለት አይደለም አሁንም ዳያስፖራው የሚያደርገውን ጥረት መቀጠል አለበት” ሲሉም አስገንዝበዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባላት የሆኑትን 14 ሴናተሮች በማነጋገር ‘ኤስ3199’ ረቂቅ ተወያይተው ለሴኔቱ እንዳያስተላልፉት የሚያደርጉትን ግፊት በተደራጀ መልኩ ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

‘ኤስ 3199’ የተዘጋጀው የኮንግረስና የሴኔት ኮሚቴዎች በአጭር ጊዜ ሁለቱ ረቂቅ ሕጎች በተመሳሳይ ሰአት ለኮንግረስና ለሴኔት ቀርበው እንዲጸድቁ ለማድረግ ነው።

‘ኤችአር 6600’ በኮንግረስ እንዲሁም ‘ኤስ.3199’ በሴኔት ከጸደቀ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመርቶ ሲፈርሙበት ሕግ ሆኖ ይወጣል።

በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ይህ እንዳይሆን የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋገር እንዲሁም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻዎችን እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አመራሮች በቅርቡ ከአሜሪካ ሴኔት የዴሞክራት መሪ ቻክ ሹመርን በማነጋገር በረቂቅ ሕጎቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ ከኦክላሃማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ለአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ሕጎቹ የሚያደርሱትን የተመለከተ ደብዳቤ አስገብተዋል።

ዳያስፖራው መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በኒው ጀርዚ ሕጉን ባረቀቁት ቶም ማሊኖውስኪ ቢሮ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ረቂቅ ሕጎቹን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም