በደረቅና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

116
አዲስ አበባ ነሐሴ 29/2010 ደረቅና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት ሊጀመር መሆኑን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለፕሮጀክቱ የሚውለው ገንዘብ በመንግስት፤ በዓለም ባንክና በዲ.ኤፍ.አይ.ዲ የሚሸፈን ሲሆን ስራው በተያዘው በጀት አመት እንደሚጀመር ታውቋል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢዜአ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ነው። ፕሮጀክቱ በደረቅና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች የሚያገጥመውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ለማሟላትና ለመስኖ የሚውል ውሃ አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ በተለይም ሶማሌ፣ አፋር፣ ቦረናና ሌሎች የውሃ እጥረት ያለባቸው ደረቃማና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። ፕሮጀክቱን ለማስጀመር መንግስት 130 ሚሊዮን ብር የመደበ ሲሆን የዓለም ባንክና ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ፍላጎት  ማሳየታቸውንም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውንም ነው ኃላፊው ያስረዱት። የፌደራልና የክልል የበላይ አመራሮችና የተለያዩ ባለሙያዎች ፕሮጀክቱን የተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም