የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሆነው የዘለቁ አገራዊ ጉዳዮችን በጋራ እልባት ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው

157

መጋቢት 13/2014 (ኢዜአ) የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሆነው የዘለቁ አገራዊ ጉዳዮችን በጋራ እልባት ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሃፊ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ 11 ኮሚሽነሮች ያሉት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ በመግባባት ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት መገንባትን አላማ አድርጎ  የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነር ጥቆማ ተቀባይና አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ሄኖክ ስዩም፤ አገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሆነው የዘለቁ አገራዊ ጉዳዮችን እልባት ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮያን የመሰለና እሴቷንም የተከተለ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ብቁ የሆኑ ኮሚሽነሮች ተሰይመው የዝግጅት ምእራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሆነው የዘለቁ አገራዊ ጉዳዮችን በጋራ እልባት ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

የውጭ አገራትን ልምድ በመቀመር የኢትዮጵያን አውድና ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ አካታችና ሁሉን አቀፍ ምክክር ለማካሄድ በማሰብ ኮሚሽኑ መቋቋሙንም አስታውሰዋል።

አገራዊ ምክክሩ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበው ለስኬቱ መላ ኢትዮጵያዊያን እንዲረባረቡ ዶክተር ሄኖክ ጠይቀዋል።

አገራዊ ምክክሩን በገለልተኝነትና በታማኝነት በመምራት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ በማሸጋገር ሂደት ከህዝብ የተጣለባቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ኮሚሽነሮቹ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም