በሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ የኃብትና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ሥምምነት ተደረገ

40

መጋቢት 13/2014 (ኢዜ)  የማዕድን ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ የኃብትና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ከአሜሪካ የዘርፉ ኩባንያ ጋር ሥምምነት ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማና የኔዘርላንድስ ስዌልና አሶሼትስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ወልፍ ፈርመውታል።

የማዕድን ሚኒስቴር በጥናትና በቁፋሮ የተገኙ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኃብት ውጤቶችን ለማልማትና በኢንቨስትመንት ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ ነው።

የነዳጅና የተፈጥሮ ኃብቱን ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ የተጠናና ዘላቂ ጥቅምን ያመዛዘነ እንዲሆን ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ ለማግኘትም መታቀዱ ተጠቁሟል።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴሩ ኔዘርላንድስ ስዌልና አሶሼትስ ኢንክ በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ዛሬ ሥምነት ላይ ደርሷል።

ኩባንያው በዘርፉ ታዋቂ ባለሙያዎችን የያዘና ለበርካታ አገራት በመሥራት ልምድ ማካበቱ ተጠቅሷል።

ኩባንያው በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ቤዚን 3500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተሰሩ የፍለጋና የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ በተፋሰሱ ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኃብት መጠን የሚያሳውቅና ኢኮኖሚያዊ ግምገማ የሚያሳይ ጥናት ያካሂዳል ተብሏል።

የኩባንያው ጥናት ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ከያዘችው የአገር በቀል ኢኮኖሚ አንፃርም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን፣ የኩባንያው አመራሮችና የማዕድን ሚኒስቴር አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም