በአምስት የጤና ተቋማት የፀረ-ሱስ ሕክምና አገልግሎት ሊጀመር ነው

141

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2014(ኢዜአ) በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ አምስት የጤና ተቋማት የፀረ-ሱስ ሕክምና አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ስለሺ ጋሩማ እንደገለጹት የትምባሆ ፣ የጫትና የአልኮል መጠጦች ምርት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ሱሶች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዛው ልክ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ገልጸው ይህም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

የሱስ የህክምና አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የጤና ተቋም አለመስፋፋት የችግሩ ተጠቂ ግለሰቦች ተደራራቢ ማኅበራዊ ችግር ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓልም ነው ያሉት።

በሱስ ችግር ለሚሰቃዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማስፋት በአምስት ሆስፒታሎች የፀረ-ሱስ ሕክምና አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቦሩ ሜዳ፣ የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ እስፔሻላይዝድ፣ የህይወት ፋና፣ መኃመድ አክሊ ሆስፒታሎችና የገፈርሳ የአእምሮ ጤና ማገገሚያ ማዕከል አገልግሎቱን ለማስጀመር ተመርጠዋል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ጤና ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ደረጀ አሰፋ በበኩላቸው የማኅበረሰቡን የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በመገናኛ ብዙኃን መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ እንዲሁም የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም መገንባት ይገኝበታል ብለዋል።

በዚህም ከስድስት ዓመታት በፊት 10 በመቶ የነበረው የአእምሮ ጤና አገልግሎት አሁን ላይ 35 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባና ድሬዳዋ በሁሉም የመጀመሪያ አሀድ የህክምና መስጫ አገልግሎት ውስጥ የአእምሮ ጤና ህክምና አገልግሎት መሰጠት መጀመሩንም ገልጸዋል።

በአእምሮ ጤና በኩል የነበረውን የመረጃ አያያዝ በማሻሻል ሁለት አመላካቾችን በመጨመር በአገሪቱ ያለው የመረጃ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም