በኦሮሚያ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ወደ 78 ነጥብ 8 በመቶ ማሳደግ ተቻለ

123

አዳማ ፤መጋቢት 13/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተካሄደው እንቅስቃሴ ሽፋኑን ወደ 78 ነጥብ 8 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ።

ሽፋኑን ማሳደግ የተቻለው  ባለፉት ሰባት ወራት ነባርና አዳዲሶችን  ጨምሮ 2ሺህ 624 የውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በመብቃታቸው እንደሆነ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

ለአገልግሎት በበቁት የውሃ ፕሮጀክቶችም  469 ሺህ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።

ይህን ተከትሎም የክልሉ  የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ሽፋን ከነበረበት  76  በመቶ ወደ 78 ነጥብ 8 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው ፕሬዚዳንቱ በሪፖርታቸው የገለጹት።

ለአገልግሎት የበቁትን ጨምሮ በተያዘው የበጀት ዓመት  መጨረሻ ድረስ በክልሉ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ሰራው መቀጠሉም ተጠቁሟል።

የፕሬዚዳንቱን ሪፖርት ያዳመጡት የጨፌው አባላት በበኩላቸው፤ በሪፖርቱ የቀረቡት ስኬቶች እንዳሉ ሆነው  ፕሮጀክቶቹ መሬት ላይ በተጨባጭ ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ማረጋገጥና ጉድለቶች ካሉ ለይቶ ማረም እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም