በምዕራብ ሸዋ ዞን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 92 ሺህ 289 ህፃናት ምዝገባ ተካሄደ

89
አምቦ ነሓሴ 29/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን ቤት ለቤት በተካሄደ እንቅስቃሴ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 92 ሺህ 289 ህፃናት ለመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን መመዝገባቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት መረጃ ባለሞያ አቶ ባይሳ በቃና እንደገለጹት ለአንድ ወር በተካሄደው የቤት ለቤት አሰሳ ለትምህርት ከተመዘገቡት ህፃናት መካከል 44 ሺህ 638 ሴቶች ናቸው። ከተመዘገቡት ህፃናት መካከል 41 ሺህ 38 የአንደኛ ክፍል አዲስ ተመዝጋቢዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በቅድመ መደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር የሚሳተፉ ናቸው፡፡ በቤት ለቤት አሰሳ የተመዘገቡት ህጻናት ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ28 ሺህ 448 ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ቁጥር ሊጨምር የቻለው ለውጡን ተከትሎ በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎች ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን ከአንድ ሺህ 900 በላይ አዲስ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችም የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምዝገባ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ከተማሪ ወላጆች መካከል በአምቦ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ አለሙ በሰጡት አስተያየት ልጆቻቸውን ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት አስመዝግበው አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። አቶ ሸለመ ጉርሜሳ አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ እንዳይቀር እየተካሄደ ባለው የቤት ለቤት ምዝገባ ከህብረተሰቡ የሚጠበቀውን ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጌታቸው ቡልቻ እንዳሉት የቤት ለቤት ምዝገባው በቤተሰብ ግንዛቤ ማነስ እድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ በቤት ወስጥ የሚቀመጡ ህፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ  በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡ መምህሩ አክለውም ለትምህርት ዘመኑ  ዓመታዊ የትምህርት ዕቅድ በማዘጋጀት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን  ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በትምህርት ዘመኑ ከ600 ሺህ በላይ ነባር የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል። በዞኑ በሚገኙ 22 ወረዳዎች 872 አንደኛ ደረጃና 84 የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም