ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም አማራጭ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሊኖራት ይገባል

63

መጋቢት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ክተቶች የሚፈጠርባትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም አማራጭ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሊኖራት እንደሚገባ በደቡብ አፍሪካ ስዌኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ ገለጹ።

በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተባባሰ የመጣው ጦርነት አንድ ወር ሊያስቆጥር ጥቂት ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል።

የጦርነቱ ጉዳይ የሁለቱ አገሮች መወራወር ቢመስልም በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በኢኮኖሚ ጉዳይ መዘዙ የበርካታ ዓለም አገሮች ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይም በአፍሪካ አገራት ላይ በዘይትና በምግብ ዋጋ ላይ የፈጠረው ቀውስ ቀላል የማይባል መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ የሃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያስከተለ ሲሆን የዓለምን የኢኮኖሚ ስርአት በማዛባትም ችግሩ ለብዙዎች ተርፏል።

በጦርነቱ የጥቁር ባሕር ወደቦች በመዘጋታቸው ምክንያት የስንዴ ምርት ዋጋ በ55 በመቶ የጨመረ ሲሆን ከእ.አ.አ ከ2008 ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከሳምንታት በፊት በአማካይ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋም ወደ 139 ዶላር አሻቅቧል።

አሁን ጦርነት ላይ የሚገኙት ሩሲያና ዩክሬን የዓለም የሱፍ ዘይት ምርት 60 በመቶ እንዲሁም ሁለቱ አገራት ለዓለም የስንዴ ገበያ 30 በመቶ ምርት የሚያቀርቡ አገሮች ናቸው።

በመሆኑም አሁን ላይ በጦርነቱ ሳቢያ በዓለም ገበያ የአቅርቦት፣ የግብይት መስተጓጎልና እጥረት አስከትሎ ቀጥሏል።

የጦርነቱን ችግር ተከትሎ እ.አ.አ በ2022 የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ድጋሚ እንዲከለስ ያስገድዳል ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።

በደቡብ አፍሪካ ስዌኔ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ፤ የሁለቱ አገሮች ጦርነት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ከባድ ምስቅልቅል መፍጠሩን ይናገራሉ።

ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓትና የንግድ ትስስር የተቆራኘ እንዲሆን በማድረጉ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚፈጠር ክስተት ሌሎችንም አገሮች መንካቱ አይቀርም ሲለም ያስረዳሉ።

በሁለቱ አገሮች ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ በተለይም የግብርና ግብአቶችና ሸቀጦች ላይ እጥረትና የግብይት ችግር ማስከተሉን ጠቅሰዋል።

በዓለም ላይ የታየው የምግብ ዋጋ ጭማሬ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋን ጨምሮ በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ማሻቀብን አስከትሏል ሲሉ ፕሮፌሰር ሙላቱ ያብራራሉ።

በመሆኑም ይህንን ጫና ተቋቁሞ ለማለፍ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የምግብ እህሎችን ማምረት፣ ውስን የነዳጅ አቅርቦትና አጠቃላይ ሃብትን በቁጠባ መጠቀም ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

በተለይም የነዳጅ አጠቃቀም ፍጆታን ከመቀነስ በተጨማሪ ከብክነት የጸዳ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

መንግስት በጦርነቱ ምክንያት የመጣውን ዓለም አቀፍ የዋጋ ጭማሬ ታሳቢ ያደረገ የበጀት ማስተካከያ ማድረግ አለበት በማለትም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

አገራዊ ፕሮጀክቶችና ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ለሚባሉት ቅድሚያ በመስጠት የወጪ ቅነሳ ላይ እርምጃ መውሰድና ያለውን የምርት አቅርቦት በተሳለጠ መልኩ ለዜጎች ማዳረስ መንግስት በመፍትሔነት ሊተገብራቸው ይገባል ብለዋል።

የበልጉን ዝናብ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አርሶ አደሩ በቶሎ የሚደርሱ የሰብል አይነቶችን ማምረት ላይ ማተኮር እንደሚገባውም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ክተቶች የሚፈጠርባትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም አማራጭ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሊኖራት ይገባል ሲሉም ፕሮፌሰር ሙላቱ አስገንዝበዋል።

የአቅርቦት ሰንሰለቱን ብዝሃ ከማድረግ ተጨማሪ የንግድ አጋሮችን በመፍጠር የሚሰፋ በመሆኑ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም የግብርና ምርታማነቷን በመጨመር ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች መቀነስ ይኖርባታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም