በኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባውቸው 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበ ነው

76

መጋቢት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባውቸው 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ "ላኒና" ተብሎ በሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

በተለይም የአገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም ቆላማ አከባቢዎችን የሚገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች የዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

በዚህም ችግሩ ለደረሰባቸው 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ በፌደራል መንግሥት፣ በአጋር አካላትና በክልሎች ቅንጅት በመቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዕለት ደራሽ ድጋፉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የያዘ መሆኑንም ገልጸው፤ አቅርቦቱ የሰውን ሕይወት ማዳን ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።

በአርብቶ አደር አከባቢዎች የእንስሳት ኃብቱ ላይም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የእንስሳት መኖ በመቅረብ ላይ መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ምትኩ ያብራሩት።   ከዕለት ደራሽ እርዳታ አቅርቦቱ ባሻገርም ለሰውና ለእንስሳት የሚሆን ውኃ በቦቴዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።  

በተጓዳኝም፤ የውሃ ተቋማትን የመጠገን፣ የአስቸኳይ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።   

"የድርቅ አደጋ በተከሰተ ቁጥር የዕለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብ ብቻ መቋቋም አይቻልም"  ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ውሃን ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ በርካታ የቁም እንስሳትን ለሞት በመዳረጉ  በተለይም የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም