በክልሉ በአይነስውሯ ተገልጋይ ላይ በደል ያደረሱ የጤና ባለሙያዎች ከስራ ታገዱ

61

መጋቢት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ህዝቦች ክልል ወላድ በሆኑ አይነስውር ተገልጋይ ላይ በደል ያደረሱ የጤና ባለሙያዎች ከስራ መታገዳቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው በጪጩ ጤና ጣቢያ ውስጥ አይነስውር በሆኑ አንዲት ወላድ እናት ላይ በታየው የአገልግሎት አሰጣጥ እንግልት ምክንያት በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር።

ነዋሪነታቸውን በዲላ ከተማ ያደረጉት ወይዘሮ ስምረት ጥላሁን አይነስውር ሲሆኑ በጤና ተቋሙ ውስጥም የተለያዩ የህክምና አገልግሎትን እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ።“ነፍሰጡር እንደመሆኔ ከምጤ ጊዜ ጀምሮ እስከምወልድበት ድረስ ማየት እንኳን ባልችልም በተቋሙ የነበሩት ሰራተኞች በጥሩ ሁኔታ እያስተናገዱኝ እንደነበር ይሰማኝ ነበር” ያሉት ወይዘሮ ስምረት ህጻኑን በሠላም መገላገላቸውን ያክላሉ።

ይሁን እንጂ ከወሊድ በኋላ ወደ ማቆያ ክፍል በማለት የተወሰድኩበትን ቦታ ማየት ባልችልም ከእናቴ ያገኘሁት መረጃ ቅር አሰኝቶኛል በማለት በተቋሙ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ አብረዋቸው የነበሩት የወይዘሮ ስምረት ጥላሁን ወላጅ እናት ወይዘሮ ብርቅነሽ ብሬ በበኩላቸው ድርጊቱ ብሎም እንድታርፍ የተደረገበት ቦታ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተገልገይዋ ላይ በተፈጠረው ችግር የጤና ጣቢያ ሃላፊውን ጨምሮ 3 ባለሙያዎች ላይ የስራ እገዳው መጣሉ ተገልጿል።በዚህ ወቅት የሚናገሩት የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ኩኡ እንዳሉት ድርጊቱን በፈጸሙት አካላት ላይ በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ ይገኛል።

ክስተቱ አሳዛኝ መሆኑን የገለፁት የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ተገኝ ታደሰ በበኩላቸው በጊዜው የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ለወ/ሮ ስምረት ጥላሁን ተገቢውን ክትትል ባለማድረጋቸው ለተፈጠረው ችግር መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ስለድርጊቱ መላውን የጌዴኦንና የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም