የሰሜን ሸዋ ዞን 40 ሚሊዮን ብር መድቦ ገበያ የማረጋጋት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

74

ደብረ ብርሃን፣ መጋቢት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የዋጋ ንረትን ለመከላከል 40 ሚሊዮን ብር መድቦ ገበያ የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ኃይሌ ዳኛቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የማይጠበቅ የገበያ ዋጋ ጭማሬ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ተስተውሏል። 

የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ከሚሰራው የገበያ ማረጋጋት ሥራ በተጨማሪ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ  መሆኑንም ጠቁመዋል።

ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ከየካቲት 2014 አጋማሽ ጀምሮ 49 ሺህ 800 ኩንታል ጤፍና ስንዴ በሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም 754 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይትና 9 ሺህ ኩንታል በርበሬ ለገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

 "ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በተደረገ ቁጥጥር 400 ኩንታል ሲሚንቶ በህገ ወጥ መንግድ ሲዘዋወር ተይዞ እንዲወረስ ተደርጓል" ብለዋል።

ገበያ የማረጋጋትና ህገወጥ እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ህገወጦችን በማጋለጥ እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በደብረ ብርሀን ከተማ የሚገኘው የእድሮች ሕብረት በጎ አድራጎት ማህበር ገንዘብ ያዥ አቶ አበበ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ገበያውን ለማረጋጋት የምግብ እህል በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ነጭ ጤፍ በኩንታል 4 ሺህ 270 ብር፣ ቀይ ጤፍ 3 ሺህ 870 ብር ለተጠቃሚዎች በመሸጥ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪዎች በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሬ የህብረተሰቡ ኑሮ እያናጋ በመምጣቱ በሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል የሚቀርበው ሸቀጥ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

መንግስት ዘይትና የተወሰኑ የፋብሪካ ምርቶች ለህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲደርስ በማድረግ የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም