የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ በአዳማ ጨፌ አዳራሽ ይጀመራል

67

አዳማ መጋቢት 11/2014(ኢዜአ)...ጨፌ ኦሮሚያ የወከለውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የጨፌው አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለፁ።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ጉባኤውን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አፈ ጉባኤዋ  "ጨፌ ኦሮሚያ የወከለውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከምን ጊዜውም በላይ እየሰራ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉን የስራ አስፈፃሚ ከመከታተልና ከመቆጣጠር እንዲሁም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ጉዳዮች በጉባኤው ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆናቸውንም አመላክተዋል።

እንደ አፈ ጉባኤዋ መግለጫ በግብርና፣ በበጋ መስኖ ልማት፣ ድርቅን በመቋቋምና በመልካም አስተዳደር በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ተጓተው ለተጨማሪ ወጪ በመዳረግ ህዝብ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው ጉዳዮች የሚፈቱበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

ጨፌው የክልሉን የስራ አስፈፃሚ አካል የስድስት ወራት ክንውን በመገምገም፣ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አዋጆችና ደንቦችን ያፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።

እንዲሁም የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን በአዲስ መልክ ለማቋቋም፣ የቡሳ ጎኖፋ የኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳትና መደጋገፍ፣ ለሰላምና ፀጥታው የጋቸነ ሲርናን ለማደራጀት የተዘጋጁ ረቅቅ አዋጆችን መርምሮ እንደሚያጸድቅም  አፈ ጉባኤ ሰዓዳ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።  

ከዚህም ባሻገር የጨፌ አባላት ስነ ምግባር፣ አሰራርና ኃላፊነትን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ በጉባኤው ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በአዳማ ጨፌ አዳራሽ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሹመቶችንም እንደሚሰጥ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም