ሚድዋይፎች የእናቶችንና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስታዋፅኦ እያበረከቱ ነው

78

አዲስ አበባ መጋቢት 09/2014(ኢዜአ) ሚድዋይፎች የእናቶችንና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስታዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ ።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማሕበር 30ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  ''ትኩረት ለእናቶች፣ ወጣቶች  እንዲሁም ለአፍላ ወጣቶች በማንኛውም ሁኔታ'' በሚል መሪ ሀሳብ አካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማህበሩ የተለያዩ ችግሮችን አልፎ ብዙ ስኬቶችንያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የእናቶችና ህጻናትን ሞት  በመቀነስ ረገድ በአገሪቷ ጉልህ አስታዋጾ  ያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የእናቶችንና ህጻናት ሞት ካለፉት ዓመታት  ጋር ሲነጻጸር  መቀነስ  እያሳየ ቢሆንም አሁንም  ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን የእናቶች የቅድመ  ወሊድና የድህረ ወሊድ ህክምና  ስርዓት  በሚፈለገው መልኩ  ባለመዳበሩ እናቶች  በቤት ውስጥ  እየወለዱ  ለሞትና  ተያያዥ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑንም አመላክተዋል።

በአገሪቱ የጨቅላ ህጻናት ሞት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ የሚድዋይፎች ማሕበር የትኩረት አጀንዳ እንዲያደርገው ጠይቀዋል።

አያይዘውም አሁን ላይ የአፍላ ወጣቶች እርግዝና ምጣኔ እየጨመረ እንደሆነና ማሕበሩ ለዚህም ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማሕበሩ ለጤና ባለሙያዎች የሙያ ስልጠና በመስጠት ተደራሽና ብቁ ሙያተኞችን መፍጠር ላይ እንዲያተኩርም አሳስበዋል ሚኒስትሯ።

በአገሪቷ ከ18 ሺህ በላይ ሚድዋይፎች ቢኖሩም ይህ ቁጥር በቂ ባለመሆኑ ቁጥሩ ወደ 29 ሺህ ለማድረስና ተደራሽነቱን ማስፋት መታሰቡንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማሕበር ፕሬዚዳንት  አቶ ዘነበ አከለ  በበኩላቸው  ማሕበሩ በመላ አገሪቱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ ነው ይላሉ።

ማሕበሩ በመላ አገሪቱ በጎፈቃደኛ እናቶችን በመመልመል ስለ ቅድመና ድህረ ወሊድ አገልግሎት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም እስከ አሁን 2 መቶ 50 ሚድዋይፍ እናቶችን በመመልመልና በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙሀንን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ ስራ ወሳኝ ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋ።
የኢትዮጵያ የሚድዋይፎች ማህበር ከ8 ሺህ 200 በላይ አባላት እንዳሉትም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም