የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በዘርፉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል ረገድ ለውጥ አምጥቷል

187

መጋቢት 08/2014 (ኢዜአ) የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በዘርፉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል ረገድ ለውጥ ማምጣቱን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የ70/30 አዋጅ ከሦስት ዓመት ወዲህ ወደ 20/80 ተሻሽሎ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።

የተሻሻለው አዋጅ  የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሚኖራቸው በጀት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነውን ለተቋማዊ አስተዳደር እንዲሁም 80 በመቶውን ለዓላማ ማስፈጸሚያ ወጪ እንዲያደርጉ ይደነግጋል፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዋናነት የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርገው የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው።

ከዚህ አኳያ በሥራ ላይ የነበረው የ70/30 አዋጅ ድርጅቶቹ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ ከማስቻል አንጻር በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ወደ 20/80 እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ የተወሳሰቡ የአሰራር ክፍተቶች የነበሩት በመሆኑ ዘርፉን በህግ ለመምራት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

በተለይም የድርጅቶቹን የአስተዳደርና የፕሮጀክት ወጪ እንደ ሥራ እንቅስቃሴያቸው ነጻ የሚያደርግ በመሆኑ  በዓላማ ማስፈጸሚያ ስም ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ እድል ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም የዓላማ ማስፈጸሚያና የአስተዳደር ወጪዎች በዝርዝርና በግልጽ ባለመቀመጣቸው የፋይናንስ መጣረስ ችግር ሲያጋጥም እንደነበር በመጠቆም።

በመሆኑም ጥናትን መሰረት በማድረግና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አዋጁ ወደ 20/80 እንዲሻሻል ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ተሻሽሎ ወደ ሥራ የገባው አዋጅ በአስተዳደርና በዓላማ ማስፈጸሚያ ወጪዎች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ግልጽ አሰራር ያስቀመጠ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በመመሪያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ግልጽ ያልሆኑና የተወሳሰቡ አሰራሮች ላይ ጭምር ማስተካከያ የተደረገበት በመሆኑ በዘርፉ ወጥነት ያለው አካሄድ እንዲፈጠር አድርጓል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ ከማሳካትና የሚያመጡትን ሃብት በአግባቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑንም እንዲሁ።

ድርጅቶቹ አዋጁን ተግባራዊ እያደረጉ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ድርጅቶቹ የሚልኩትን ዓመታዊ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ በመስክ ጉብኝትና በተለያዩ መንገዶች የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መመሪያው የአሰራር ጉድለት በሚፈጥሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያዝም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ3 ሺህ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም