ምክር ቤቱ ሴቶች በሥራ ፈጠራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው

54

መጋቢት 9/2014/ኢዜአ/ ሴቶች በሥራ ፈጠራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመለከተ።

ምክር ቤቱ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ከሥራ ፈጣሪና ቢዝነስ አንቀሳቃሽ ሴቶች ጋር ተወያይቷል።    

በውይይቱ ላይ ስኬታማ የቢዝነስ ሕይወት ያሳለፉ ሴቶች ተሞክሯቸውን ያጋሩ ሲሆን ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድም ቀርቧል።   

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት  ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ ሴቶች የሥራ ፈጠራ አቅማቸው እንዲጎለብት የተለያዩ ፕሮክቶችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው።   

ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት /ጂ አይ ዜድ/ ጋር በመተባበር የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ዘርፍ የሥራ ፈጠራ ክህሎት፣ የቢዝነስ እቅድ ዝግጅት ላይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።   

እንደ ወይዘሮ መሰንበት ገለጻ ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን ማነቃቃት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ወሳኝ ነው፤ ሴቶች በዘርፉ የሚያከናውኑት ተግባር በተሻሻለ ፖሊሲ ለመደገፍም እየተሰራ ነው።  

"ሴቶችን ማበረታታት ካልቻልን፤ጤናማ እና አምራች ካላደረግናቸው ስለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እኩልነት ማለማችን ብዙም ትርጉም የለውም ነው" ያሉት።   

በከተሞች ያለውን የሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ ሴቶችን ያሳተፈ ተግባራት ማካሄድ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።     

"ለዚህም በሴቶች የሚመራ ቢዝነስ ተቋማትን ማብዛት ትልቅ ሚና አለው" ያሉት ወይዘሮ መሰንበት የተወዳዳሪነት፣የፋይናንስና የአቅርቦት ችግሮችን መፍታት ላይ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።    

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሥራ ፈጣሪሴቶች በበኩላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባቋቋሙት የቢዝነስ ተቋም በአብዛኛው ሴቶችን ቀጥረው እያሰሩ ነው።    

ሴቶች በሚያቋቁሙት ተቋም የሚፈጥሩት የሥራ እድል እንዲሰፋ የቦታ አቅርቦት ላይ መሥራት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም