በዱብቲ ሆስፒታል የኦክሲጂን ማምረቻ ተገንብቶ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ

61

ሠመራ፤ መጋቢት 09/2014(ኢዜአ) ኢንተርናሽናል ሪፕሮዳክቲቭ ሄልዝ ትሬኒንግ የተባለ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአፋር ክልል ዱብቲ ሆስፒታል ያስገነባው የኦክሲጂን ማምረቻ ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀመረ።

የኦክሲጅን ማምረቻውን መርቀው  ስራ ያስጀመሩት የክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባና የድርጅቱ መስራችና  ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሃ ናቸው።

በተጨማሪም ድርጅቱ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በዱብቲ  ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ  የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ፤ዱብቲ ሆስፒታል በክልሉ ህክምና በመፈለግ የሚመጡ በርካታ ነዋሪዎችን ተቀብሎ የሚስተናግድ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይም አሁን ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ችግር ጋር ተያያዞ  ሆስፒታሉ ያለበት ጫና ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው፤በዚህም ምክንያት ታካሚዎችን ለማስተናገድ የክፍልና ህክምና ግብአት እጥረት እንዳጋጠመው ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የኦክሲጅን እጥረት በሆስፒታሉ አንዱ ጎልቶ የሚታይ ችግር መሆኑን ጠቁመው፤ ዛሬ የተመረቀው የኦክስጅን ማምረቻ ችግሩን ለማቃለል እንደሚያግዝ  አስረድተዋል።

በተጨማሪም አጠቃላይ ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠው የማስፋፋያ ግንባታ  በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለታካሚው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል ርዕስ መስተዳድሩ።

ለዚህ ስራ ቁልፍ ባለድርሻ ለሆኑት ለኢንተርናሽናል ሪፕሮዳክቲቭ ሄልዝ ትሬኒንግ ድርጅት መሰራችና ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሃና ባልደረቦቻቸው በክልሉ ህዝብና መንግስት  ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሮፌሰር ሰናይት  በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው በስነተዋልዶ ጤና ለረጅም ዘመናት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ አሁን ሃገሪቱ ካጋጠማት የጸጥታ ሁኔታ  ጋር ተያይዞ ያሉትን  የጤና አገልግሎት ችግሮችን ለማቃለል የሚያግዝ ስራዎች  ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው የዱብቲ ሆስፒታል የኦክሲጅን ማምረቻ  የዚህ ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማምረቻው በቀን 200 ሲሊንደር ኦክሲጅን ያመርታል ነው ያሉት።

ለግንባታውም  ድርጅታቸው 60 ሚሊዮን ብር  ወጪ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ጫናዎችን ለማቃለል በተለይም ለእናቶችና ህጻናት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚካሄደው የማስፋፊያ ግንባታ በስድስት ወራት  ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃና እስከ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር  ወጪ እንደሚፈጅ አብራርተዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም