የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ

92

ሀዋሳ መጋቢት 9/2014 (ኢዜአ) ምክር ቤቱ ከህዝብ የተሰጠውን አደራ ለመወጣት የጀመራቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ አስታወቁ።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

አፈ- ጉባኤዋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት በጠንካራ አደረጃጀት በመምራት የክትትልና ቁጥጥር ስራ አከናውኗል።

የክልሉን እድገት ለማፋጠንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በበጋ መስኖ የተሰራው የስንዴ ምርት ውጤታማ መሆኑን ገልጸው ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከክልል እስከ አርሶ አደር ማሳ ድረስ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን ገልጸዋል።

በክልሉ የተመደበውን ውስን ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የተሰራው ስራ የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው "ከህዝቡ ጥያቄ አንጻር ያሉትን ውስንነቶች በመፍታት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች በቀጣይ ትኩረት ይደረግባቸዋል" ብለዋል።

በማህበራዊ ዘርፍ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሠጣጥ ያሉ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ ግድፈቶችን ማረም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምክር ቤቶች በተለይም በመልካም አስተዳደር፣ልማት፣ፍትህ መረጋገጥ ረገድ የሚነሱ ጠያቄዎች በተገቢው ምላሽ እንዲያገኙ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በትጋት ሊወጡ እንደሚገባ አመልከተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን በመገምገምና በመደገፍ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ለውጥ እንዲመጣ የጀመሩት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"በቀጣይም በግብርናው ዘርፍ የምርት እድገት እንዲጨምር፣ የፕሮጀክቶች ግንባታ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ፣የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል፣የወጣቶችና የሴቶች የስራ እድል ፈጠራ እንዲጠናከር ይሰራል" ብለዋል ።

ሀገራዊ የምክክር መድረክ በተሳካ መንገድ ተካሂዶ የታለመው ጠንካራ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም ደግሞ የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።

የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚደረጉ ችግሮችን ለመፍታት ከክትትልና ቁጥጥር ጀምሮ አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ የክልሉን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ያለፉት ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እያደመጠ ይገኛል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም