ወጣቶች በግብርና ልማት ሥራ ላይ በአዳዲስ የፈጠራ ኃሳቦች በስፋት ሊሰማሩ ይገባል

90

መጋቢት 09 2014(ኢዜአ) ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ ኃሳቦችን በማፍለቅ በግብርና ልማት ሥራ ላይ በስፋት መሠማራት እንዳለባቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

በሚኒስቴሩ የአዳዲስ ሥራ ዕድሎችና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አለም ፀሃይ ደርሶልኝ፤ ግብርናን ማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለውጭ ንግድ አስተዋፅፆ የላቀ ነው ብለዋል።

ዘርፉን ለማዘመንና የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማግኘት መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ግብርናው በቀላሉ ለማዘመን የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

በተለይም ደግሞ ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለዘርፉ ልማትና እድገት መትጋት እንዳለባቸውና ለዚህም ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድጋፍ ያድርጋል ነው ያሉት።

በተለይም የአግሮ-ፕሮሰሲንግና ዘርፍ አገሪቱ ያልተጠቀመችበት መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በማፍለቅ በስፋት ሊሰማሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ያሉ ዘርፎችን ምን አይነት ሙያ ማዳበር አለባቸው የሚለውን ማጥናቱን ገልፀው እነዚህም በአገሪቱ የ10 ዓመት የልማት እቅድ ተካተዋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልገው በእቅዱ የተካተተ መሆኑን አንስተው ለዚህ ተግባር የወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤት ወጣቶች በበኩላቸው፤ የግብርናውን ዘርፍ ልማት ለመደገፍ የሚያደርጉትን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።    

የአዞላ ፊልድ ሥራ አስፈፃሚ ጌድዮን ተፈራ፤ አዞላ ከተሰኘ ውሃ ላይ ከሚበቅል ተክል ለእንስሳት የሚሆን የዶሮ መኖ ማዘጋጀት ችሏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከሆኑ ሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሃሳቡን ማበልፀግ መቻሉን የተናገረው ጌዲዮን የፈጠራ ሥራው ለዶሮ እርባታ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብሏል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን አቅም በመጠቀም ከዘርፉ የምትገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንዲቻል ወጣቶች ዘርፉን የሚያዘምኑ የፈጠራ ሃሳቦችን በስፋት ሊያቀርቡ እንደሚገባ ገልጾ ዘርፉን ለማዘመን ባለሃብቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቋል።   

ከእንሰት ለተለያዩ ምግቦች የሚውል ዱቄት ይዞ የቀረበው የብራይት ማኑፋክቸሪንግ መሥራች ሰለሞን መገርሳ በበኩሉ ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ወደ መፍትሄ በመቀየር የሥራ ፈጣሪ መሆን እንደሚችሉ ይናገራል።

በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎችን መደገፍ እንደሚገባም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም