የመንግስት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ ሂደታቸውን ግልጽና ፈጣን ማድረግ አለባቸው

137

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 09/2014 (ኢዜአ) የመንግስት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ ሂደታቸውን ግልጽና ፈጣን ማድረግ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።

ተቋማቱ ለሕብረተሰቡ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው ተብሏል።

የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ዓ.ም ላይ እንደሰፈረው ዜጎች መረጃ የማግኘት ሕገ-መንግስታዊ መብት እንዳላቸውና የመረጃ ባለቤቶች መሆናቸውን ይደነግጋል።

የመረጃ ነፃነት ይዞት ከተነሳው ዓላማ አንፃር በአግባቡ ቢተገበር በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ተመልክቷል።

ከጠቀሜታዎቹ መካከልም ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፤ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል፤ ፍትህን ማስፈን እንዲሁም የዜጎች መብትና ጥቅሞችን ማስከበር ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተቋሙ የመረጃ ነጻነትን ተፈጻሚነት የመከታተል እና የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህም በመሆኑ ተቋሙ እስካሁን ባደረገው ግምገማና ምልከታ መሰረት የመንግስት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ ሂደት ግልጽና ፈጣን መሆን አለበት ይላሉ።

ዋና ዕንባ ጠባቂው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዳግም ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ በኃላ የተወሰነ መሻሻሎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

ሆኖም አሁንም የመረጃ አሰጣጥ ሂደቱ ግልጽነትና ፍጥነት የሚጎድለው በመሆኑ ይህ ችግር መፈታት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለይም በየተቋሙ ያሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ማነቃቃት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የትኛውም የመንግስት ተቋም በሕዝብ እና ለሕዝብ እስከተቋቋሙ ድረስ በግልጽነት መረጃን ሊሰጡ እንደሚገባም አሳስበዋል ዋና ዕንባ ጠባቂው።

የተቋማት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃ ለሚጠይቅ አካል የመስጠት ኃላፊነት ሳይሆን ግዴታ እንዳለባቸውም መዘንጋት የለባቸውም ብለዋል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቋሚ ግንኙነት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንደ አስፈላጊነቱ ምላሽ እንዲያገኙም እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁኔታው በመረጃ ነጻነት አዋጅ ላይ በተቀመጠው መሰረት ሕዝብ አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኝ የሚያግዝ ነውም ብለዋል።

ተቋሙ ዋነኛ የመንግስት የመረጃ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ተደራሽነቱን ለማስፋት ዘመን ያፈራቸው መረጃ ማሰራጫ ዘዴዎችን እንደሚጠቀምም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም