መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ በትኩረት እየሰራ ነው

54

መጋቢት 9 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት ዛሬ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ እና ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው የህንድ ባለሀብቶች እና ከህንድ የኢንቨስትመንት ፎረም አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ህንዳውያን ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ከፀጥታ እና ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት ውስጥ ከአሁን በፊት ለውጭ ባለ ሀብቶች ክፍት ያልሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ጭምር ክፍት ማድረጓን አስታውሰዋል።

የሕንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅትም መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መልካም አብነት ያላቸው ናቸው ብለዋል ።

ከባለሀብቶቹ ለተነሱት ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደ ሀገር ለሁሉም ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲፈጠር ይሰራል ነው ያሉት።

የህንድ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት መፍታት ከቻለች በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉር ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን አቅም አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከባለሀብቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ጊዜ ሰጥቶ በማዳመጥ ለክፍተቶች እልባት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ከውይይቱ በመረዳታችን ደስተኞች ነን ብለዋል።

አሁን ላይ ከ6 መቶ በላይ የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ከውጭ ጉዳይ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም