የዓለም ጤና ድርጅት ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶችን አደርሳለሁ ካለበት ቀን ቀደም ብሎ ከመንግስት ፈቃድ አግኝቷል

82

መጋቢት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም ጤና ድርጅት ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶችን አደርሳለሁ ካለበት ቀን ቀደም ብሎ ከመንግስት ፈቃድ ማግኘቱን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የህክምና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ፈቃድ እንደተከለከለ አስመስለው ማቅረባቸው ተገቢነት የሌለውና የአገርን ገጽታ ለማጠልሸት ዓላማ ያደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የዓለም ጤና ድርጅት መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ለጤና ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ ከመጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ድረስ ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ጥያቄ ማቅረቡን አንስተዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርም የዓለም የጤና ድርጅት 95 ሜትሪክ ቶን መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል እንዲያጓጉዝ ፈቃድ እንዲሰጠው መጋቢት 05 ቀን 2014 ዓ.ም ለኮሚሽኑ በደብዳቤ መጠየቁን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የዓለም ጤና ድርጅት የህክምና ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ እጀምራለሁ ካለበት ከመጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ፈቃድ አግኝቷል፡፡

በመሆኑም ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ እንዳላገኘ አስመስሎ መናገሩ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ያቀረቡት ቅሬታ እውነታውን ያላገናዘበ፣ የአገርን ገጽታ ለማጠልሸት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አውሮፕላኖች አማካኝነት ወደ ትግራይ እርዳታ እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ነው ያረጋገጡት፡፡

በዛሬው እለት ብቻ የምግብ ነክ ቁሳቁሶችን የጫኑ 20 የጭነት ተሽከርካሪዎች እና 3 ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ ጉዞ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም