የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ እና ዳኞች ሃብታቸውን አስመዘገቡ

68

መጋቢት 08 ቀን 2014(ኢዜአ) የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና የሥራ ኃላፊዎች በአዲሱ የዲጂታል ሃብት መመዝገቢያ ሲስተም ሃብታቸውን አስመዘግበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፤ በዛሬው እለት የሃብት ምዝገባ ያከናወኑ ሲሆን ህብረተሰቡን በፍትሃዊነት ለማገልገል ሙስናን መከላከል አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው፤ በፍርድ ቤቶች ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን የመከላከል ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በፍርድ ቤቶች የአንድ መስኮት አገልግሎትና አዲስ የዲጂታል ፋይል ዝውውር ተግባራዊ በማድረግ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በሥሩ የሚገኙ ተቋማት ለሌሎች አርዓያ ለመሆን በዲጂታል መመዝገቢያ ቀዳሚ ተመዝጋቢ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ፤ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ሙስናን የመከላከል ጥረት ቢደረግም አሁንም ችግሩ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የመንግስት ሰራተኞች በማንዋል ሀብታቸውን ያስመዘገቡ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ አሰራሩን ያዘመነ የዲጂታል ምዝገባ መጀመሩን ገልጸዋል።

የዲጂታል ሃብት ምዝገባ በእጅ ከሚደረገው ምዝገባ አንፃር በጥራት፣ በፍጥነትና፣ በግልጸኝነት የተሻለ መሆኑን አብራርተው አዲሱ አሠራር የመረጃ ጥራትና ተደራሽነትን የሚጨምር፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈንና የጥቅም ግጭትን ለመከላከል እንደሚረዳም ጠቁሟል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ማናቸውም ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች ሀብት እንዲያሳውቁና እንዲያስመዘግቡ፣ የሕግ ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን፤ ኮሚሽኑም የመዘገበውን መረጃ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት እንደተሰጠው በግልጽ ተደንግጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም