ፈለገ አዋሽ በነሐሴ ሠማይ!

156
አየለ ያረጋል/ኢዜአ/ አዋሽ ድንበር አቋርጦ ከአገሩ አይሰደድም፤ አዋሽ ባይተዋርነት አይሰማውም፤ ወረት አሻፍሮት አይኮበልልም፤ ግንድ ይዞ አይዞርም፤ አዋሽ እንደ ወንድሙ ፈለገ ግዮን ማደሪያ ቢስ አይደለም፤ ሐሴቱና መከፋቱ እንደ መቀነት በተጠመጠማት እናቱ ጉያ ነው። አዋሽ ጥማቱንና ድሎቱን በግልፅ ተናግሮ ከመሸበት ያድራል። የእናቱን ደጃፍ ሲቃኝ አምሽቶ የድንቅነሽ ባድማን ትራሱ አድርጎ ያሸልባል።ይሄ ምግባሩ ያስደመመው የትውልድ ቀዬ ወዳጁ ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ 'የወንዙን ልጅ አዋሽ' እንዲህ ይጠይቀዋል! …. አጥንትህን ምድረ በዳ፤ ሀሩሩ እሚመዘምዝህ ሜጫ ቋጥሮ ሸዋ ፀንሶ፤ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ ከዳዳ ምንጭ አሩሲ፤ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን፤ አዳል ሞቲ ሸህ ሽሉን ይዞ ከከረዩ ማታ ሐራ፤ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ እንደ ወላድ ሳይታረዝ፤ ከነጽንሱ አረህ ሰምጦ በምድረ በዳ ጉሮሮ፤ በርሀ ላንቃ ተውጦ አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ፤ ላይገላገል ሸምጥጦ እስከ መቸ ይሆን አዋሽ ተስፋ መቁረጥ እማታውቅ?…. አዋሽ በደንዲ (ምዕራብ ሸዋ) ቆፈን ይጸነሳል። በሸዋ ተረተሮች ይፋፋል። በጉራጌ ሸጦች ይንቦራቻል። በአርሲ ወንዞች ይጎለምሳል። በከረዩ ማታሐራ እስከ አፋር ምድረ በዳዎች ሲያንጎራጉር ያመሻሻል። በአፋር ሀሩር፣ በጥንተ ሰብዕ ቅሪት መገኛው ምስራቅ ኢትዮጵያ እቶን ተኮራምቶ አርጅቶ አቤ ሐይቅ ሕይወቱ ያልፋል። እንዲህ ነው! አዋሽ ተቆጣም ተለሳለሰ፤ በረሃ አረስርሶ ያልፋል እንጂ ከአድባር፣ ከአውጋሩ እግሩ አይነቀልም። ምሥራቅ አፍሪካዊቷ የውሃ ማማ (ምድረ ቀደምቷ-ኢትዮጵያ) ዓመታዊ የዝናብ መጠኗ ከፍተኛ ነው። የገፀ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብቷም በ12 ተፋሰሶች ይፈሷል። እርሷ ግን የተትረፈረፈ የውሃ ሀብቷን በቅጡ ባለመምሯቷ ተጠምታለች፣ ገጿን ማስዋብ ተስኗት ቆይታለች። እናም ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎቷ የተፏሰሶቿ አበርክቶቱ እምብዛም ነው። የውሃ ሀብት አስተዳደር ፖሊሲ ብትቀርጽም፤ እስካሁን የተፋሰስ ባለስልጣን ተቋቁሞላቸው ስራ የጀመሩት ሶስቱ (አዋሽ፣ አባይ፣ ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች) ተፋሰሶች ብቻ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የአዋሽ ተፋሰስ ግንባር ቀደም ነው። መልክዓ ምድራዊ አቀማምጡ ለልማት ምቹ ነውና በአንጻራዊነት ከሌሎች የተሻለ ተፋሰስ ነው ማለት ያስደፍራል። አዋሽ የሚሊየኖች ተስፋና ስጋት የአዋሽ ተፋሰስ ጎራማይሌ ባህሪ አለው። አየር ንብረቱ ደጋ፣ ወይናደጋ፣ ቆላና በረሃ ነው። በአዋሽ ወንዝ የሚመራው ተፋሰሱ ኦሮሚያን፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ አማራ ክልሎች ያካልላል። አዋሽ ሁለቱ ግዙፋን ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ንዑስ ተፋሰሶችን አቅፏል። ይህን ሁሉ መልክዓ ምድር ያቀፈው ተፋሰሱ ለሚሊየኖች ተስፋና ስጋት ነው። ከአስር ዓመት በፊት በ1999 ዓ.ም በወጣ መረጃ ብቻ ከ18 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፤ ከ43 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት በተፋሰሱ ይኖሩ እንደነበር ተረጋግጧል። አዋሽ ተፋሰስ ምቹ መልክዓ ምድር፣ የእርሻ መሬትና የውሀ ፍሰት ታድሏል። አዋሽ በኢንዱስትሪ ቀጣናነቱም ፊታውራሪ ነው። ለመስኖ፣ ለመጠጥ ውሃ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ፣ ለአሣና ለመዝናኛ አገልግሎት ፍላጎቱ ከሁሉም ተፋሰሶች በተሻለ ሁኔታ ለምቷል። አዋሽ ከምንጩ (አዋሽ ቦሌ ቀበሌ) እስከ አቤ ሐይቅ 1 ሺህ 250 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን 116 ሺህ ስኩዌር ካሬ ሜትር የሚሰፋው፣ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ባለቤት ነው፤ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የተፋሰሱ መሬት በመስኖ ለምቷል። አዋሽ-ከቆቃ በላይ፣ አዋሽ- አዋሽ፣ አዋሽ-ሃሊዳቢ፣ አዋሽ-አዳይቱ፣ አዋሽ-ተርሚናልና አዋሽ-ኢስተርን ተብሎ በስድስት ንዑስ ተፋሰሶች ይከፈላል። ከሶስት ዓመታት በፊት በአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በተፋሰሱ ከ73 ሺህ በላይ የውሃ ተጠቃሚዎችም አሉ። በተፋሰሱ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በምግብና መጠጥ፣ በብረታ ብረትና ግንባታ ዕቃዎች፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያና ሌሎች መስኮች የተሰማሩ ከ11 ሺህ 800 በላይ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት ነው። ይሁንና ሌላኛው የአዋሽ መልክ በጎርፍ አደጋ የታጀበ፣ በስጋት የዳመነ ነው። በሕዝብ ብዛት፣ በከተሞችና ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ከእርሻ ልማትና አካባቢ መራቆት፣ የውሃ ብክለት፣ ከአፈር ጨዋማነት፣ የድርቅና ጎርፍ ማጥለቅለቅ ለተፋሰሱ መከራና ስጋቶች ናቸው። ከዚህ በፊትም በበርካታ አካባቢዎች ላይ ያስከተለው አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ የትየሌለ ነው። የባለስልጣኑ መረጃዎች እንድሚጠቁሙት፤ ባለስልጣኑ ለችግሩ መፍትሔ የ10 ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቷል። ዕቅዱም በተፋሰስ ልማት፣ በውሃ ምደባ፣ በውሃ ጥራት፣ በጎርፍና ድርቅ መከላከል፣ በመረጃ አስተዳደርና ኮሙኒኬሽን ስድስት ዘርፎች ያተኩራል። በባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጀርመን እንደሚያብራሩት፣ በንዑስ ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተግባራት (የስነ አካላዊ፣ ስነ ሕይወታዊ) በየዓመቱ መተግበር ጀምረዋል። በዚህ ዓመትም የብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ቅድመ ትንበያን መሰረት በማድረግ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። በተለይም የዘንድሮ ክረምት በስርጭትም ሆነ በመጠን ከፍተኛ ዝናብ እንደሚዘንብ ቀድሞ ተገምቶ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሳሉ። ባለስልጣኑ ባሉት 72 የሃይድሮሎጂ ማዕከላት የወንዙን ፍሰት እየተቆጣጣረ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰለሞን፣ የስጋት ቦታዎችን በመለየት በላይኛው ተፋሰስ 16 ኪሎ ሜትር፣ በመካከለኛው 105 ኪሎ ሜትር፣ በታችኛው ደግሞ የ11 ኪሎ ሜትር የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየስ፣ ነባር ቦዮችን መጠገን፣ ደለል ማውጣትና ተያያዥ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ያም ሆኖ ግን የአዋሽ ወንዝ ሙላት ስጋት ከፍተኛ ነውና ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ያስገነዝባሉ። በያዝነው ወርኃ ነሐሴ የዝናብ መጠኑ መጨመሩን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ በተለይም የቆቃና ከሰም ግድቦች መሙላታቸውን ይናገራሉ። እናም ባለስልጣኑ የውሃ መጠኑን ለመቀነስ ከግድቦቹ ውሃ ስለሚለቀቅ የወንዙ አካባቢው ነዋሪ ማኅበረሰቦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። እስካሁንም በላይኛውና መካከለኛው የተፋሰሱ ክፍሎች በከባድ ዝናብ ሳቢያ በተለይም በደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ባሉ የተወሰኑ ወረዳዎች የአዋሽ ወንዝ የመሙላትና ከወንዝ የመውጣት ሁኔታ መከሰቱን ገልጸዋል። ለአብነትም በሰበታ ሀዋስ፣ በኢሉ፣ በቦራ፣ በሊበን ጩቃላ፣ በሎሜ፣ በአዳማ፣ በቦሰት፣ በወንጂ፣ በፈንታሌ፣ መርቲ እና ጀጁ ወረዳዎችን አንስተው፤ በተጠቀሱት አከባቢዎች ነዋሪው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። እስካሁን ባለው የክረምቱ ጊዜያት ከባድ አደጋ አለመከሰቱን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ “ባለፈው ሳምንት ግን በሊበን ጩቃላ ወረዳ ለጊዜው ቁጥራቸው በመጣራት ላይ ያሉ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት የመፈናቀል አደጋ ገጥሟቸዋል'' ብለዋል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ተወስኖ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። በተመሳሳይ በመካከለኛው አዋሽ የአሚባራ፣ ዱለቻ፣ ገለኣሎና ገዋኔ ወረዳዎች እንዲሁም በታችኛው አዋሽ ዱብቲ፣ አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች ወንዙን ተጠግተው የሚኖሩ ማኅበረሰቦችና የመስኖ ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም