ከወጭ ንግድ ባለፉት ሰባት ወራት ለተገኘው 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ምርት ገበያው የላቀ ድርሻ ነበረው

94

አዲስ አበባ፣  መጋቢት 8/2014 /ኢዜአ/   ከወጭ ንግድ ባለፉት ሰባት ወራት ለተገኘው 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የላቀ ድርሻ እንደነበረው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርት ገበያው  ለወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን የግብርና ምርቶች እያገበያየ ይገኛል።

ከዚህ ቀደምም የቡና፣ ሰሊጥ፣ ቀይ እና ነጭ ቦሎቄ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ሲያገበያይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ካለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ወዲህ አረንጓዴ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ ሽንብራ እና ኑግ የመሳሰሉ ተጨማሪ የግብርና ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓት እንዲገቡ በማድረግ ሰፊ የገበያ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የተሻለ የወጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶች፣ የማዕድን ውጤቶችንና ሌሎችም የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ግብይት ስርዓት ለማስገባት ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ምርቶችን ወደ ገበያ የማስገባት አቅምን ማሳደግ መቻሉም በተለይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩ ለሚያመርተው ምርት አስተማማኝ የገበያ እድል ለመፍጠር ጉልህ ሚና ያለው እንደሆነም አንስተዋል።

የወጪ ንግዱን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንዲጨምር በማስቻል ረገድ እንዲሁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው፤ በተያዘው ዓመት ሰባት ወራት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የግብይት ስርዓቱን ለማዘመን ተደራሽነቱን በማሳደግ ምርት መቀበያ መጋዘኖችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምርት ገበያው በመላ ሀገሪቱ ግብይት የሚፈጸምባቸው 23 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን በሚዛን አማን እና ቴፒ ከተሞች አዳዲስ የምርት መቀበያ መጋዘኖችን በመክፈት ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።

በአንድ ማዕከል በአዲስ አበባ ብቻ ይደረግ የነበረውን የግብይት ስርዓት አሁን ላይ በክልሎች በኤሌክትሮኒክስ የተገናኙ የግብይት ማዕከላት ቅርንጫፎችን በመክፈት ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርት አቅራቢዎች፣ አምራቾችና የህብረት ስራ ማህበራት ወደ ዋናው ማዕከል መምጣት ሳይጠበቅባቸው በየክልሎቻቸው እንዲገበያዩ በማድረግ የግብይት ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚረዳ እንደሆነም ጠቁመዋል።  

በተጨማሪም ምርት ገበያው የግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ከአቅራቢዎች ግብይት የሚፈጽሙበት ልዩ የግብይት መስኮት ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም