የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የስነ-ምግባር ችግር የታየባቸውን 146 የፖሊስ አመራርና አባላት ከተቋሙ አሰናበተ

80

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የስነ-ምግባር ችግር የታየባቸውን 146 የፖሊስ አመራርና አባላት ከተቋሙ አሰናበተ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ የኮሚሽኑን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የፖሊስን ሙያዊ ዲስፕሊን በመተላለፍ የተለያዩ ጥፋቶችን የፈፀሙ 146 የፖሊስ አመራርና አባላት ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል።

በዲስፕሊን የታነጸና ህዝብን ለማገልገል የሚሰራ የፖሊስ ሃይል የመገንባት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከተማዋን የሚመጥን የፖሊስ ሃይል ለማደራጀት የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ባልተገባ መንገድ እንዲሰናበቱ የተደረጉ ከ400 በላይ የፖሊስ አባላት ዳግም ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ኮማንደር ፋሲካ ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት ጥቅም ላይ ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በህዝብና በፖሊስ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በቁጥጥር ሂደቱ በርካታ የብሬን፣ ክላሽ፣ ሽጉጥና መሰል ጥይቶች እንዲሁም የተለያዩ መሳሪያዎች መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

ከጦር መሳሪያዎቹ ጋር የተያዙት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ተደርጎ በህግ ፊት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በከተማዋ በግለሰቦች እጅ የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን ለማወቅ በተደረገው ምዝገባም ከ2 ሺህ 300 በላይ የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ 23 ሺህ ሽጉጦች እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ መሳሪያዎችና ጥይቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩ ከሚችሉ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሮች ጋር በተያያዘ 9 ሚሊየን ብር እንዲሁም የተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዙን ጠቅሰዋል።

በጸጥታ ኃይሎች እና በህብረተሰቡ የተቀናጀ የጸጥታ ስራ በከተማዋ የተዘጋጁ የተለያዩ ኩነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር መከናወናቸውንም ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም