ኢዜአ እና ኦቢኤን በኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትብብር መሥራታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

71

መጋቢት 8/2014 /ኢዜአ/  ኢዜአ/ እና ኦቢኤን በኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትብብር መሥራታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የሁለቱ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት በተለይም በአገር የማዳን እና የህልውና ዘመቻ እንዲሁም በመልሶ ግንባታና ዜጎችን መልሶ በማቋቋም  በትብብር ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት መረጃዎችን በመለዋወጥና ህዝቡ እንዲጠቀምባቸው ከማድረግ አንጻር በጋራ ሰፊ ሥራዎችን ማከናወናቸውን አስታውሰው አሁንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በህግ ማስከበሩ ወቅትና በህልውና ዘመቻው ጊዜ ሁለቱ ተቋማት በሚዲያው ዘርፍ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን እንደሰሩ አስታውሰው፤ በቀጣይም አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።  

በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ሚዛናዊ፣ ፈጣንና እውነተኛ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።  

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዋና ዳይሬክተር ዝናቡ አስራት በበኩላቸው፤ ሁለቱ ተቋማት የአገር ህልውና ለማስጠበቅ የፈጸሙት ተግባር በታሪክ የሚዘከር መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የትብብርና አብሮ የመሥራት ልምድ በማስቀጠል ለአገርና ህዝብ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይም በምርመራ ዘገባ ሌብነትን በማጋለጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማጋለጥ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።   

ሁሉቱ የሚዲያ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ እያስገነባ ላለው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የስቱዲዮ መሳሪያ የማሟላት ሂደት ኦቢኤን የማማከር እና ሌሎች እገዛዎችን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።   

ሁለቱ ተቋማት የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ የነበራቸውን ጥምረት በልማት፣ ህብረተሰቡን በማንቃት እና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ለመረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ ያነጋገርናቸው የኢዜአ እና ኦቢኤን ሠራተኞች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያዊያን እሴቶች በማጎልበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማጠናከር ሂደት ሁለቱ ሚዲያዎች በትብብር ይሰራሉ ብለዋል።

ኢዜአ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመሆን በአዳማ ከተማ የፎቶ አውደ- ርዕይ አዘጋጅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም