ቤተክርስቲያኗ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ-ጸሎትና ቀብር በሠላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቀረበች

87

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ጸሎትና ቀብር በሠላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቀረበች።

የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በህይወት ዘመናቸው ቤተክርስቲያንን ሲያገለግሉ የኖሩ አባት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ ሥርዓተ ጸሎቱና ሥርዓተ ቀብራቸው የቤተክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ በሰላም መፈጸሙን ገልጸው፤ ከዕለተ እረፍታቸው እስከ ቀብራቸው ፍጻሜ ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሐዘን ተካፋይ የነበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።

በተለይም ብፁዕነታቸው ከ26 ዓመታት በኋላ ወደሚወዷት አገራቸው ተመልሰው ሽኝታቸው ባማረ ሁኔታ እንዲፈፀም ላደረጉት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ሲኖዶሱን አንድ ለማድረግ ለደከሙ ሁሉ ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ማቅረቧን ተናግረዋል።

ከዕለተ እረፍታቸው እስከ ቀብራቸው ፍጻሜ ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሐዘን ተካፋይ የነበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።

የቅዱስነታቸው ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ ቀብር በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ላደረጉ የጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤቶችን ጨምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ የመንግሥት አስተዳደር አካላት፣ የፀጥታ ተቋማት፣ ሚዲያ እና ሌሎች ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምዕመናንን በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም አመሥግነዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት አባቶች፣ የእህት ቤተክርስቲያን ተወካዮች እንዲሁም በርካታ ህዝበ ክርስቲያን በተገኙበት መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መፈጸሙ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም