ምክር ቤቶቹ አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ወሰኑ

125
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2010 አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የጋራ ውሳኔ አሳለፉ። ምክር ቤቶቹ የቆጠራው ጊዜ እንዲራዘም በተናጠል ውሳኔ አሳልፈው እንደነበር ይታወሳል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው ስብሰባ የቆጠራው ጊዜ በአንድ ዓመት እንዲራዘም በ90 ድጋፍ፣ በ10 ተቃውሞ እንዲሁም በ3 ድምጸ ተአቅቦ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቶቹ ዛሬ ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በማድረግ አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዲራዘም የጋራ ውሳኔ አሳልፈዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ በጋራ ስብሰባው ላይ ቆጠራው እንዲራዘም የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል። የህዝብና ቤት ቆጠራ በየአስር ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የሚገኘው መረጃ አገሪቷ ለምታካሂደው ፈጣንና ዘላቂ ልማት ወሳኝ ሚና አለው። ቆጠራው መካሄዱ 'የልማት እቅዶችን ለማዘጋጀት፣ ለመገምገም፣ ለፍታዊ ሀብት ክፍፍል፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለህዝቡ ለማቅረብ፣ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እንዲሁም ለክትትል የጎላ ጠቀሜታ አለው' ብለዋል አፈ ጉባዔው። ይህንን ከግምት በማስገባት ከፍተኛ በጀት ተይዞ ቆጠራውን በ2010 ዓ ም ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። ከቆጠራው የሚገኘው መረጃ ጥራት ያለው፣ አስተማማኝ፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል የሚካሄድበት ጊዜ ለሁሉም አመቺ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በቅርቡ የተከሰቱት የነዋሪዎች መፈናቀል፣ የጸጥታ መደፍረስና መሰል ችግሮች ቆጠራውን በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዳይካሄድ አድርጓል። በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ቆጠራውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን በተሟላ መልኩ ማካሄድ ባለመቻሉ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የተሻለ ሆኖ መገኘቱን አቶ ያለው ተናግረዋል። የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ቆጠራው እንዲራዘም ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው አቶ ያለው ጨምረው  የተናገሩት። ዝርዝር ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለ2011 ዓ ም እንዲራዘም ለጋራ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበው እንዲጸድቅ ተደርጓል። በዚህ መሰረት የጋራ ምክር ቤቱም የውሳኔ ሀሳቡ በአንድ ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ ቁጥር 1/2010 ሆኖ እንዲራዘም ወስኗል። በጋራ ስብሰባው ላይ 320 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ 98 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም