በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች የጽዳት ንቅናቄ ሊካሔድ ነው

76

መጋቢት 7/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ በ569 ትምህርት ቤቶች ከፊታችን አርብ ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የጽዳት ንቅናቄ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው።

የመዲናዋ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲና የትምህርት ቢሮ በጋራ የጽዳት ንቅናቄውን በተመለከተ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለመጡ ርዕሳነ-መምህራን የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ለማ፤ የጽዳት ንቅናቄው ከፊታችን አርብ ጀምሮ በየሳምንቱ በ569 ትምህርት ቤቶች ይካሄዳል፡፡

የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ ጤናማ አኗኗር እንዲኖር መሰረት መሆኑን ተማሪዎች እንዲገነዘቡ ለማስቻል ንቅናቄውን በትምህርት ቤቶች አካባቢ ማካሔድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢ ንጽህና ጉድለት በመማር ማስተማር ስራ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ፅዳትን በዘላቂነት ማከናወን እንደሚገባ የትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ማህበረሰቡ በጽዳት ዘመቻው በመሳተፉ ለውጥ ለማምጣት አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በየሳምንቱ ከሚያደርጉት የጽዳት ዘመቻ ባሻገር ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው አካባቢ በመውጣት ለህብረተሰቡ ስለ ንጽህና አጠባበቅ ግንዛቤ እንዲሰጡ መታሰቡንም ተናግረዋል ፡፡

በምክትል ከንቲባ መዐረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ፤ ንጹህ አካባቢን እውን ማድረግ አስተዳደሩ በትኩረት ከሚሰራባቸው መስኮች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የሚካሔዱ የጽዳት ዘመቻዎች ጽዱና ውብ አካባቢን ለመፍጠር የሚተጋ ትውልድ ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለሚያስመዘግቡ ትምህርት ቤቶች እውቅና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

ኤጀንሲው እና የትምህርት ቢሮው በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ በእለቱ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም