በኦሞ ኩራዝ አካባቢ 2 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እየሰራ ነው

154

መጋቢት 07/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በኦሞ ኩራዝ አካባቢ 2 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኮርፖሬሽኑ በመንገድ፣ በድልድይ፣ በመስኖ ልማት፣ በግድብ እና ህንፃ ግንባታ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመስኖ እርሻ የሚውሉ በርካታ የግድብ ስራዎችን መስራቱንም ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በመስኖ ልማት የገነባውን ልምድና አቅም በመጠቀም በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ውጤት ለማምጣት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም በኦሞ ኩራዝ  አካባቢ 2 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የዝግጅት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይ በዚሁ አካባቢ 7 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት መታቀዱን ጠቁመው ተቋሙ መዋቅር አደራጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል።

የጊዳቦ ግድብ የመስኖ ስራን በሶስት ወራት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ  የአካባቢውን አልሚዎች በስፋት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ አሁን እየሰራቸው ካሉ ስራዎች መካከል አብዛኛዎቹ ለውጭ ስራ ተቋራጮች የሚሰጡ እንደነበሩ አስታውሰው በተቋሙ በመሰራቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያዳነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጪ አገራትም ተጉዞ የግንባታ ስራዎችን እያከናወነ የተሻለ ጥቅም ለአገር እያገኘ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም