ከተሞች ፍላጎትና አገልግሎትን ለማመጣጠን በስትራቴጂካዊ ዕቅድ መመራት አለባቸው - ሚኒስቴሩ

60

ሚዛን፣ መጋቢት 07/2014 (ኢዜአ) ከተሞች ፍላጎትና አገልግሎትን ለማመጣጠን በስትራቴጂካዊ ዕቅድ መመራት እንደሚገባቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ።

ሚኒስቴሩ በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ ስልጠና በሚዛን አማን ዛሬ መስጠት ጀምሯል።

በሥልጠናው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  የካፋ፣ ሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

ሚኒስትሯ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የከተሞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በስትራቴጂክ ዕቅድ መምራት ይገባል።

"የከተሞች መበራከት በአግባቡ መምራት ከተቻለ አዎንታዊ ትርጉም አለው" ብለዋል።

"ነገር ግን በከተሞች የሚታየው የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ውስብስብነትና የመሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊ አለመሆን መጨናነቅ በመፍጠር አሉታዊ ጎኑን አስፍቶታል" ሲሉም አመልክተዋል።

በተለይ ከገጠር የሚፈልሱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ከተሞች ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማውጣት መመራት እንደሚያስፈልጋቸው ወይዘሮ ጫልቱ አስገንዝበዋል።

መንግሥት የከተሞችን የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማሟላት ስለማይችል ሚኒስቴሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 2 ሺህ 500 ከተሞች መካከል 117 ታዳጊ ከተሞች በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (UIIDP) ታቅፈው የመሠረተ ልማት ሥራ እየተሰራባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት በፕሮግራሙ ከታቀፉ ከተሞች መካከል ሦስቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ፕሮግራሙ ከተሞች የሚታዩባቸውን ጉድለቶች በመሙላት ተወዳዳሪ  እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አመራሩ በራስ አቅም ከተሞችን ለማልማት  በቁርጠኝነት እንዲሰራ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ የክልሉ አዲስነትን  ታሳቢ በማድረግ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በነበረው ኢፍትሐዊ የሀብትና የመሠረተ ልማት ተደራሽነት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ እድሜ ጠገብ ከተሞች ሳይለሙ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

አሁን በተፈጠረው ዕድል ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በራስ አቅም ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸው፤ ከአቅም በላይ የሚሆነውን ከሚኒስቴሩ ጋር በመመካከር የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

"ክልሉ የሀብት ችግር እንደሌለበት ያወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከተሞችን ከአጎራባች የገጠር ቀበሌዎች ጋር በኢኮኖሚና መሠረተ ልማት በማስተሳሰር ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ይሰራል" ብለዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የማታዓለም ቸኮል በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች የውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎችም የአገልግሎት እጥረት ያለባቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የታቀፉ የሚዛን፣ ቦንጋና ቴፒ ከተሞች በማዘጋጃ ቤት በኩል በሚያገኙት የድጎማ በጀት እያለሙና ሥራ አጥነትን መቀነሳቸውን አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ ተጨማሪ  ከተሞችን በፕሮግራሙ እንዲያቅፍ ጠይቀዋል።

በሥልጠናው አመራሩ በዘርፉ ጠንክሮ የሚወጣበትን አቅም ይፈጥርለታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም