የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያካሄደ ያለው የተቋሙ መዋቅራዊ ማሻሻያ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታወቀ

50

መጋቢት 7/2014/ኢዜአ/ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያካሄደ ያለው የተቋሙ መዋቅራዊ ማሻሻያ ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታወቀ።

በቅርቡ ምደባ ከተሰጣቸው አምባሳደሮች የተወሰኑት ወደ ተመደቡበት አካባቢ ሳይሄዱ፤በአገር ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ  ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም ገልጿል። 

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የዜጎቿን መብትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ጥቅሞች የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እያራመደች ትገኛለች።

ፖሊሲው በተለይ በንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፍ፣ በአገር ሉዓላዊነትና ገፅታ ግንባታ፣ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብት ማስከበር ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።  

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በሰጥቶ መቀበል መርህ የሌሎችን መብትና ጥቅም በማክበር እንዲሁም በእኩልነትና በመከባበር መንፈስ የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እየሰራች እንደሆነም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ለውጦችን ታሳቢ ያደረገ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትግበራ ላይ መሆኗንም አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

በአገር ውስጥም የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና አገራዊ መግባባትን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ፖሊሲን የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ባሉበት ምህዳር በሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅና አገርን የሚመጥን ተቋማዊ መዋቅራዊ ማሻሻያ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለምና በአህጉር ደረጃ ያሉ ሁኔታዎችን በማጥናት ፈታኝ ሁኔታዎችና መልካም እድሎችን በመለየት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር መከናወን ያለባቸው ስትራቴጂዎች መቀየሳቸውንም ነው የጠቆሙት።

ለስትራቴጂው ተፈጻሚነት በዋናው መስሪያ ቤትና በውጭ በሚገኙ ኤምባሲዎች የመዋቅር ማስተካከያ በማካሄድ ብቁ ዲፕሎማቶች እና አጠቃላይ የሰው ኃይል የማሟላት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የሰው ኃይልና የዲፕሎማቶች ምደባ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በአግባቡ በመረዳት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የመተንተን ብቃትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችው የአምባሳደሮች ምደባ ተደራሽነትንና ብቃትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ይችላሉ ተብለው የታሰቡ አምባሳደሮች መመደባቸውን ነው ያስረዱት ።

በምደባው የተካተቱ የተወሰኑ አምባሳደሮች ወደ ተመደቡበት አካባቢ ሳይሄዱ፤ በአገር ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር እንዲሰሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

በተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ ኤምባሲዎች ደግሞ በአነስተኛ የሰው ኃይል ሰፊ አካባቢዎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

መዋቅራዊው ማሻሻያ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ያስታወቁት ቃል አቀባዩ ወደ ፊት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም