በሚቀጥሉት ሶስት ወራት የ150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ሊፈጸም ነው

80

መጋቢት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት ሶስት ወራት በመንግስት ልማት ድርጅቶች በኩል የ150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ሊፈጽም መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፤ የምግብ ዘይት ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ብልጽግና ፓርቲ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት የሸቀጦች የዋጋ ንረትን፣ የአቅርቦት እጥረትን በአጠቃላይ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በልዩ ትኩረት ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

በመሆኑም የምግብ ዘይት እጥረትና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በባቡር ትራንስፖርት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በማህበራት በኩል በስርጭት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት ቀሪው 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በጅቡቲ በኩል ይገባል ብለዋል።

የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራቾችን አቅም ለማሳደግ አፋጣኝ የማምረትና የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።

በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል አፋጣኝ ግዥ ተከናውኖ አገር ውስጥ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በቀጣይ ዓመታት በሚከፈል የዲፈር ዲ.ኤል.ሲ (Differ DLC) የክፍያ ስርዓት የምግብ ዘይት ለማስገባት ፍላጎት ላላቸው የንግድ ድርጅቶች ፈቃድ መሰጠቱንም አመልክተዋል።

የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እና የኩታ ገጠም ግብርናን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው የግብርና ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ ገብቶ መሰራጨቱን አስታውሰው በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት ስምንት ወራት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ(ፍራንኮ ቫሉታ) ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከታክስ ነጻ የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የማጓጓዣ ነዳጅ ድጎማ መደረጉንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም